1647504161172

መንግስት ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ለማጋለጥ እያሳየ ያለውን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ወደ ተግባር ለመቀየር እንሰራለን ሲሉ የፌደራል ስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽነር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ ተናግረዋል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው ኮሚሽነሩ በሀገሪቱ ተቋማዊ የመሰለውን የተደራጀ ሌብነት እና ብልሹ አሰራር በማጋለጥ ከከፍተኛ ባለስልጣናት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ተጠያቂነት ለማስፈን እንሰራለን ብለዋል።

ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ እንዲሁም ጠንካራ ተቋም ለማድረግም አደረጃጀቱን እየፈተሸ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ተቋማዊ አቋሙን በማስተካከልም በመንግስት እየታየ ያለውን ቁርጠኝነት ለመጠቀም እንሰራለን ብለዋል ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ፡፡

የመረጃ ስርአትን ማሳደግ እና ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራትም ቀጣይ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።

የሀብት ምዝገባ ሂደትም ወደ ዲጂታል መቀየሩ ተመላክቷል ሲል ኤፍ ቢ ሲ ዘግቧል።