1647573409031

በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የዎላይታ ሶዶ ዲስትሪክት በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ 105 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ዕዳ ለማስመለስና 82 ሚሊዮን ብር ብድር ለስራ አጥ ወጣቶች መልሶ ለማሰራጨት ማቀዱ ተገለፀ።

በዕቅዱ ዙሪያ የዋናው መ/ቤት ደጋፊ ባለሙያዎች፣ የዲስትሪክቱ አመራሮችና ባለሙያዎች እና የ24 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ስራ አስኪያጆች ውይይት አካሂደዋል፡፡

በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና መ/ቤት የሰው ኃብት ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታፈሰ ኦሎሎ የሶዶ ዲስትሪክት በፈረንጆቹ አቆጣጠር እስከ ማርች 31/ 2022 ድረስ 105 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ዕዳ በማስመለስ 80 በመቶ ለስራ አጥ ወጣቶች ብድር ለማሰራጨት ላቀደው ዕቅድ ዋና መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ተቋሙ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ በመሆኑ ከዚህ በፊት ለስራ አጥ ወጣቶች የተሰጠውና ውዝፍ ሆኖ የቆየው ገንዘብ በአግባቡ ተመላሽ ተደርጎ በአሁኑ ወቅት የስራ ፍላጎት እያላቸው የመነሻ ካፒታል ችግር ላጋጠማቸው ወጣቶች እንዲሰራጭ የባለድረሻ አካላት መድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የሶዶ ዲስትሪክት እና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አመራሮችና ባለሙያዎች ያላቸው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ታፈሰ ለዚሁም የዋና መ/ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የሶዶ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ያይና በበኩላቸው ዲስትሪክቱ ከዚህ በፊት ለስራ አጥ ወጣቶች ተሰራጭቶ ውዝፍ ሆኖ የቆውን ዕዳ በማስመለስ እና ለሌሎች ስራ አጥ ወጣቶች በቢዝኔስ ዕቅዳቸው መሠረት መልሶ በማሰራጨት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መጣውን የሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዲስትሪክቱ ውዝፍ ዕዳ በማስመለስ ዙሪያ ከቀናት በፊት ከፍትህ ተቋማትና ከስራ ዕድል ፈጠራ ም/ቤት ጋር ያካሄደው ሰፊ ውይይትና የጋራ ስምምነት ዕቅዱን ለማሳካት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የጠቀሱት አቶ ተመስገን 24ቱም ቅርንጫፍ ጽቤቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር ለዕቅዱ ስኬት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

ተቋሙ ደንበኞች የወሰዱትን ብድር ቅድሚያ በድርድር የሚያስመልስ ሆኖ ሳለ ለመክፈል ፍቃደኛ ያልሆኑ ደንበኞችን በህግ የሚያስከፍል በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የህዝብ ሀብት የሆነውን ገንዘብ ተበድረው ያስወዘፉ አካላትን ለማስመለስ ለሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዳንዶቹ እንዳሉት ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን መልካም የስራ ግንኙነት በመጠቀም ዕቅዱን ለመሳካት ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

እንደ ዞን መኮ ዘገባ በወይይት መድረኩ ላይ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ዋና መ/ቤት ደጋፊ ባለሙያዎች፣ የሶዶ ዲስትሪክት አመራር አካላትና ባለሙያዎች እና የ24 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሥራ አስኪያጆች ተሳትፈዋል፡፡