“በደቡብ ክልል አዲስ የተፈጠሩ ሁለት ክልሎች መንግስታዊ እንግልት በማስቀረቱ የሌሎች መሠል ጥያቄዎችን የህዝቦችን አንድነትና ሰላምን በሚያስጠብቅ መልኩ የህዝብን ፍላጎት መሠረት ተደርጎ ምላሽ ይሰጣል” የክልሉ አፈጉባኤ
የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ጉባዔው በርካታ ሀገራዊ ኩነቶች በተስተዋሉበት ማግሥት የሚደረግ ጉባዔ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው በዋናነት መላው ኢትዮጵያዊያን በሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣውን ጥቃት የውስጥ ባንዳና የውጭ ጋላቢ ኃይል ጫና በመቋቋም ኢትዮጵያዊያን ዛሬም እንደ ትላንቱ የማንበረከክ ህዝብ መሆናችንን ለዓለም በሳየንበት ወቅት የሚደረግ ጉባኤ መሆኑ ነው ብለዋል፡፡

ክብርት አፈ ጉባኤዋ አክለውም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ሀገርና ህዝብን የማስተዳደር ዕድል ያገኘው ብልጽግና ፓርቲ በምርጫ ያገኘውን ድል እንደ ዕድል በመጠቀም ህዝብን በላቀ ትጋትና ቁርጠኝት በማገልገል ቃሉን በተግባር ለመግለጽ በመተለም ጉባዔ በማካሄድ ከፈተና ወደ ልዕልና ለመንደርደር የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ባስተላለፈበት ማግስት የሚካሄድ ጉባኤ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ ለብሔራዊ መግባባት አደናቃፊ የሆኑ በርካታ ተንከባላይ ሀገራዊ ውስብስብ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን በመግለጽ ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ባለበት ጊዜ የሚካሄድ ጉባኤ መሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያዊያንና የክልላችን ህዝቦች ሀብት የሆነው የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል የማመንጨት ሥራ በጀመረበት ወቅት የሚደረግ ሲሆን ለዚሁም መላው ኢትዮጵያዊያንና የክልላችን ብሔር በሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የምክር ቤት አባላት እንኳን ደስ ያላችሁ እንኳን ደስ ያለን መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ምክር ቤቱ ለክትትልና ቁጥጥር ሥራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር እንቅስቃሴ እያደረገ መቆየቱን የገለጹት ክብርት አፈ ጉባኤዋ በምክር ቤቱ የተደራጁ ቋሚ ኮሚቴዎች የግማሽ ዓመቱን የአስፈፃሚ አካላት ዕቅድ አፈፃፀም በዝርዝር የፈተሹ ሲሆን የግምገማ ሂደቱም የቀረበውን የጹሑፍ ሪፖርት በማየት ብቻ ሳይሆን የመስክ ምልከታም ጭምር የታከለበት እንዲሆን ተደርጎ በመስክ ምልከታም ሆነ በጹሑፍ በቀረቡ ጉዳዮች ዝርዝር እይታ በማድረግ ተገቢ ግብረ መልስ የተሠጠበት መሆኑንም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
በየጊዜው እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት እንደ ሀገርም እንደ ክልላችን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ቢኖሩም ካለው ውስብስብ ችግር አንፃር ገና መቀረፍ ያለባቸው ቀሪ የቤት ስራዎች ይኖሩናል፡፡ ለዚህም መንግስት፣ አምራች፣ አከፋፋይ ነጋዴዎችና ሸማቹ የህብረተሰብ ክፍል ተቀናጅቶ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በአገራችን ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ፣ የዜጎች ወንድማማችነትን የሚያጎለብትና የጋራ አገራዊ ራዕይ የሚሰንቅ፣ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችንና ግጭትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል፣ እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ ውጤታማ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ በሁሉም አካላት ዘንድ ቁርጠኝነት እንዲፈጠርና ፣ለሒደቱ ስኬታማነትም ምክር ቤቶችና መላው ማህበረሰቡ በጎ አስተዋጽኦውን እንዲያበረክት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የለውጡ መንግስት በየጊዜው የሚስተዋሉ የህዝቦች የመልማት፣ የመደራጀትና የመዋቅር ጥያቄዎችን በሰከነ መልኩ እየመለሰ እንደሚገኝ ገልጸው በክልላችን ከዚህ ቀደም ሁለት የክልል መዋቅር ጥያቄዎች ተመልሰው ህዝቦች መንግስታዊ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩን አውስተዋል፡፡

ቀሪ የመዋቅር ጥያቄዎችን ለመፍታትም መንግስታችን ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው የህዝቦችን አንድነትና ሰላሙን በሚያስጠብቅ መልኩ በበሰለና በሰከና ሁኔታ በመወያየት የህዝብን ፍላጎት መሠረት ባደረገ አግባብ ምላሽ የሚሠጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡
ስለሆነም ህዝባችን የመንግስትን አቅጣጫ ተረድቶ ከልዩ ልዩ ውዥንብሮችና ሰላማችንን ከሚያደፈርሱ አጀንዳዎች በመታቀብ የመንግስትን ውሳኔ በትዕግስት እንዲጠባበቅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
