
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዝቦች ወንድማማችነትና እህትማማችነት መርህ የተመሰረተ የስምምነት ዉጤት ነዉ፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን የመሰረቱት ዞኖች ተቀራራቢ ታርክና ስነ ልቦና፤የጋራ ጥያቄና አብሮ ተባብሮ የማደግ ፍላጎት ያላቸዉ ህዝቦች ናቸዉ፡፡ሁሉም ዞኖች ለዚህ ክልል ዕዉን መሆን የማይተካ ሚና ተጫዉተዋል፡፡ የትግሉ ባህር ከአካባቢ አካባቢ የሚለይ ቢሆንም በክልል የመደራጀት ጥያቄ የሁሉም ህዝቦች ጥያቄ ነበር፡፡
በዚህ ሂደት ለብቻ ከመደራጀት በጋራ መደራጀትና ተያይዞ ማደግ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የሁሉም ዞኖች ምክርቤቶች የተናጠል ጥያቄዎቸዉን ወደ ጎን በመተዉ በወንድማማችነትና እህትማማችነት መንፈስ ስድስቱም አካባቢዎች አንድ ለመሆን ታርካዊ ዉሳኔ በማሳለፍ ፈጠን ያለ ምላሽ እንዲሰጥ ታግለዋል። በዚህም ኢ-ፍትሃዊነት ያንገበገባቸው፣የመልካም አስተዳደር እጦት ያብከነከናቸዉና ተያይዞ ማደግን በሩቅ ያለሙ ወንድማማች ህዝቦች ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ የራሳቸዉን ክልል በራሳቸዉ ነጻ ፍላጎት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትሎ እዉን አድርጓል።
የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የነበረዉ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ስድስቱም ዞኖች አንድ ላይ ሆነዉ ክልል ለመመስረት ሲሰማሙ በዉይይታቸዉ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን እያስቀደሙ ከአሁን ቀደም በነበረዉ ክልል የተዛነፉ ጉዳዮችን በአዲስ መልክ ለማረም በመስማማትም ጭምር ነዉ፡፡ከእነዚህ ጉዳዮች አንዱ አዲስ የሚመሰረተዉ ክልል ብዝሃ ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት የተደረሰዉ ስምምነት ነዉ፡፡ይህ ስምምነት በህገ መንግስት ዉስጥ መካተት እንዳለበት ስለታመነ የክልሉ ህገ መንግስት ሲረቀቅ በሁሉም አካባቢዎች በህዝብ ተወካዮች ተተችቶና ሀሳቡም ተቀባይነት አግኝቶ በህገ መንግስት ዉስጥ ተካቶ የስምምነታችን ሰነድ የሆነዉ ህገ መንግስታችን በህዳር 14/2014 ዓ.ም ጸድቆ ስራ ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡
በመሆኑም በህገ መንግስቱ ከብዘሃ ዋና ከተሞች አደረጃጀት ጋር ቀሪ ስራዎችን ሰርቶ ለመጨረስ ኃላፊነት የወሰደዉ የክልሉ መንግስት ከሁሉ አጀንዳዎች ትኩረት ሰጥቶ ቀደም ሲል ዉይይት የተደረገባቸዉን ጉዳዮችንም ይዞ ከሁሉም ዞኖች በተወከሉት ኮሚቴዎች አማካይነት ወደ ጫፍ ለማድረስ እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም ሂደት ዉስጥ ስለ ብዝሃ ማዕከላት አደረጃጀት አስቀድሞ ክልሉ ከመመስረቱም በፊት የዉጭ ሀገር ተሞክሮች የተቀመሩቡት የክልሉን ምስረታ በበላይነት በሚያስተባብረዉ ኮሚቴ በተደጋጋሚ ዉይይት የተደረገበት አጀንዳና መሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት የተደረሰበት የፌዴራል መንግስትም ድጋፍና ምክርም የታከለበት ነዉ፡፡
ነገር ግን ስራዉ ለሀገራችን አዲስ እንደመሆኑ መጠን ብዝሃ ዋና ከተሞች እስርበርስ ስለሚኖራቸዉ ግንኙነት፤በብዘሃ ዋና ከተማነት የተመረጡ ከተሞችና ሌሎች ቀሪ ከተሞች በፍትሃዊነት ስለሚያደጉበት መንገድ፤የብዘሃ ዋና ከተሞች ክፍፍል መሰረት ማድረግ ስላለበት መርሆችና መስፈርቶች ዙሪያ የሁሉንም አካባቢዎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ወንድማማችነት መርህን በሚያረጋግጥ መንገድ መፈጸም ስላለበት ምክንያታዊ ጊዜ ወስዷል፡፡
በዚህ ሂደት አስቀድሞ ዉይይት የተደረገበትንና ህገ መንግስታዊ መሰረት የያዘን ጉዳይ አንዳንድ ህዝብን የማይወክሉ አካላት በህዝቦች መካከል ጥርጣሬን ለመፍጠር በየማህበራዊ ሚዲያዉ የሀሰት መረጃና ጥቅም የሌለዉ ዘመቻ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡በዚህ ጉዳይ ላይ የክልሉ መንግስት ያለዉን የማያዋላዳ አቋምና በክልላችን ህገ መንግስት ዉስጥ የተቀመጠዉን ለማስፈጸም ያለዉ ቁርጠኝነት በተለያዩ የህዝብ መድረኮችና ሚዲያዎች ሲገለጽ መጥቷል፡፡አሁንም ይህን የብዘሃ ዋና ከተማ ጉዳይ በፍጥነት ጨርሶ ተግባራዊ ማድረግ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ እንዳለ የክልላችን ህዝብ ተገንዝቦ ለዚህም ተግባራዊነት አስፈላጊዉን ትብብር እንዲያደርግ እንጠይቃለን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን ጉዳይ እንደኮርኳሪ አጀንዳ በመዉሰድ በወንድምና እህት ህዝቦች መካከል ጥርጣሬና የብሽሽቅ ፖለቲካ በማራመድ በሂደትም ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲያመራ እየሰሩ ያሉ አካላት ከድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ የክልሉ መንግስት አበክሮ እያሳሰበ የክልላችንም ህዝቦች በየማህበራዊ ሚዲያዉ ለሚነዛዉ ኢ-ምክንያታዊ ወሬ ጆሮ ባለመስጠት እንዲታገል ጥሪ እናቀርባለን ሲል የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዘግቧል፡፡