
አብዴን ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ተወህዶ ትግሉን ለመቀጠል ውሳኔ ማሳለፉን የንቅናቄው ሊቀመንበር ተናገሩ፡፡
የንቅናቄው ሊቀመንበር አቶ ሐሰን መሐመድ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት አብዴን ሰሞኑን ባካሄደው ጉባኤ የአርጎባ ህዝብ መብቱ በተሟላ ሁኔታ ሊከበር የሚችለው ከብልፅግና ጋር ሲዋሃድ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ጉባኤው በሰፊው ከተወያየ በኋላ ንቅናቄው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር እንዲዋሀድ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ውይይቶች የሚደረጉ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ሐሰን፣ ውህደቱ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ አብዴን ህልውናው የሚያበቃ ይሆናል ብለዋል፡፡
የባህር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን እንደዘገበው ጉባዔው ከዚህ በተጨማሪ 27 የንቅናቄውን ማዕካላዊ ኮሚቴና 11 ሥራ አሰፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን የመረጠ ሲሆን ንቅናቄው በልዩ ሁኔታ ከስራ አስፈፃሚዎች መካከል 5ቱ ሴቶችና 3ቱ አካል ጉዳተኞች እንዲሆኑ መደረጉን ሊቀመንበሩ አመልክተዋል፡፡
ከ27 ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት መካከል ደግሞ 20ዎቹ አዳዲስ ሲሆኑ ከስራ አስፈፃሚዎች 8ቱ አዲሶቹ መሆናቸውንም አቶ ሐሰን ለዶይቼ ቬሌ ነግረዋል፡፡ የአርጎባ ብሔረሰብ በአማራና በአፋር ክልሎች ይገኛል፡፡