1648192258150

ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ላለፉት 16 ወራት ግጭት ውስጥ የቆየው ህወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ግጭት ለማቆም እንደሚስማማ ገለጸ።ህወሓት ይህን ያለው ትናንት ሐሙስ መጋቢት 15/2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲደርስ ለማስቻል ግጭት ለማቆም መወሰኑን ካስታወቀ በኋላ ነው።

የፌደራሉ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ “በእጅጉ ሊያሻሽል” ስለሚችል እና “በቀጣይ ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ ለግጭቱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል” ተስፋ በማድረግ መሆኑን ገልጿል።መንግሥት ይህ ውሳኔ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ “በትግራይ ክልል የሚገኙ አማጺያን ከማንኛውም ጥቃት እንዲታቀቡና በኃይል ከያዟቸው የአጎራባች ክልል አካባቢዎች እንዲወጡ” ጠይቋል።

ይህን ተከትሎ ህወሓት ባወጣው መግለጫ ላይ በበቂ መጠን እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ የሚደርስ ከሆነ ጥሪውን እንደሚቀበል ገልጿል።በትግራይ ካለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እና ተቀባይነት ባለው ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታው የሚደርስ ከሆነ “የትግራይ መንግሥት ግጭት ለማቆም ቁርጠኛ ነው” ብሏል። ቢቢሲ