
የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት አካባቢዎች በምግብ እጥረት የተጎዱ ወገኖች ርዳታ እንዲደርሳቸው በማሰብ የተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉ በአማራ ክልል ነዋሪዎች ዘንድ ድጋፍ እና ተቃውሞ ተንጸባርቆበታል። ውሳኔው ትክክለኛ ርምጃ ነው ሲሉ አንዳንድ የአማራ ክልል ነዋሪ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ ከሕወሓት ባህሪ አንፃር ውሳኔው ተግባራዊ ላይሆን ይችላል በሚል ጥርጣሬያቸውን ያስቀመጡም አሉ። ውሳኔውን የነቀፉም አሉ። ዶይቼ ቬሌ (DW) የመተማን፣ የደሴን፣ የቆቦን፣ የጉና ቤጌምድርንና የጋዝጊብላ ነዋሪዎችን አስተያየት ጠይቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ትናንት በባሕር ዳር የተጀመረው የአማራ ክልል ምክር ቤት አመልክቷል።
ካለፈው ጥቅምት 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ሚሊዮኖች ለእንግልትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል፣ ብዙዎች ለከፋ የምግብ እጥረትም ተጋልጠዋል። ምንጭ የጀርመን ድምፅ ሬድዮ