1648213027899

ባለቤትነቱ የቻይና ባለሀብቶች የሆነና የኤሌክትሪክና ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻዎችን መልሶ በማሰባሰብ፣ በመገነጣጠልና በየፈርጃቸው መድቦና መልሶ በማምረት ቁሶቹ ተመልሰው ለጥቅም እንዲውሉ ከሚሰራ ዓለማቀፍ ድርጅት ጋር በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ከፍቶ ወደ ስራ ለመግባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ሰሞኑን ተካሂዷል።

በ26 ሚሊዮን ረሚምቢ (የቻይና የን) የተመዘገበ ካፒታል ወደ ስራ የገባው ይህ ተቋም መቀመጫውን በቻይና ቢያደርግም በአሁኑ ወቅት በሀገረ ጀርመን፣ ማሌዢያና ሲንጋፖር ቅርንጫፎች በመክፈት የዳበረ ልምድ ያካበተ ሲሆን በኢትዮጵያ ያለውን አቅም በመመልከትም የሀገሪቱ ህግ የሚፈቅድ ከሆነ በኢትዮጵያ የ”ኢ-ዌስት ፓርክ” በመክፈትና ከሌሎች የአፍሪካ ጎረቤት ሀገራትም ጭምር በማስገባትና መልሶ በማምረት ወይም ምርቶቹን ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ ፍላጎት እንዳለ በካምፓኒው የስራ ሀላፊዎች ገለፃ ተደርጓል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ ህግ መሠረት የስራ ፈቃድ፣ የማምረቻ ቦታና ምናልባትም የሚፈቀድ ከሆነ ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት ግብአቶቹን ማስገባት የሚያስችል ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ባለሀብቶቹ በኢትዮጵያ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ህግ መሠረት ሀብታቸውን በኢትዮጵያ ስራ ላይ እንዲያውሉ ከኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር የማገናኘት ሚናን የተጫወቱት የቀድሞ የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትርና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ክቡር  አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም ናቸው።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር ጌታሁን ጋረደው እንግዶቹን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው በጉዳዩ ዙሪያ ከእንግዶቹ ጋ በዝርዝር የተወያዩ ሲሆን በቀረበው የመነሻ ውይይት ላይ ተመስርቶም በቀጣይ  ከሚመለከታቸው ሌሎች ተቋማት ጋር በመነጋገርና የሀገራችንን የዘርፉን ህግጋት በዝርዝር በማየት ውሳኔ ለመስጠት እንደሚሰራ ከምስጋና ጋር ገልፀውላቸዋል።