የዎላይታ ዘመን መለወጫ (ጊፋታ) በዓል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት አፈጻጸም የማጠቃለያ ሪፖርት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገመገመ

የዎላይታ ዘመን መለወጫ የጊፋታ በዓል አከባበር በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት አፈጻጸም የማጠቃለያ ሪፖርት ከፌደራል፣ ከክልልና ከዞን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተገምግሟል፡፡

የዎላይታ ዘመን መለወጫ (ጊፋታ) በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ ተመዝግቦ ዘላቂ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲደረግለት የቅርሱ ባለቤት ከሆነዉ የዎላይታ ህዝብ በየጊዜዉ ይቀርብ እንደነበረ ይታወሳል።

ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት የዞኑ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ከዎላይታ ዞን ዋና አስተዳደር ጋር በመሆን ለክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቶ በ2013 ዓ.ም ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል፡፡

በትችት መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሂሩት ኃይሉ በንግግራቸው ህብረተሰቡ ጊፋታና ሀይማኖት በፍጹም የማይገናኙ መሆኑን እንዲያውቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዞኑ አስተዳደሪ ሥራዉ ውጤታማ እንዲሆን የበጀት ድጋፍ ማድረጉንና እንዲሁም የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለሥራው ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አክሊሉ ለማ የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጊፋታን በዩኔስኮ ለማስመዘገብ ሁሉ አቀፍ ጥረት እያደረጉ ያሉ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን በወላይታ ህዝብና በአስተዳደሩ ስም አመሰግነዋል፡፡

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ አቡቶ ኦኑቶ በበኩላቸው ባለድርሻ አካላት ተደራጅተው መስራታቸውን አድንቀው ለቀሪ ሥራዎች ይበልጥ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምርምና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ ጊፋታ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖረው ለቀሪ ሥራዎች ከፕሮፌሽናል ሰዎች ጋር በመቀናጀት እንዲጠናቀቅና ዩኒቨርስቲው የራሱን ድርሻ እንደሚወጣም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በዩኔስኮ ማይዳሰሱ ቅርስ አመዘጋገብ ዙሪያ እና በሌሎችም ጉዳዩ ለሚመለከታቸዉ አካላት ስልጠና በመስጠት ሥራ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ከ300 በላይ ሰዎች ይዉንታቸዉን የገለጹበት የህዝብ ፊርማ በ2014 ዓ.ም የጊፋታ በዓል በተከበረበት ወቅት በብሔሩ ተወላጅ በሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በማስጀመር በሁሉም ወረዳ እና የከተማ አስተዳደር በመገኘት በተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አማካይነት ተሰብስቧል፡፡

ከግምገማዉ በኋላ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ቀጣይ ተግባራትን በአጭር ጊዜ ዉስጥ በመፈጸም ያለቀ ሥራ ለኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ለማስረከብ እንዲቻል ዋናዉን ዕቅድ በመከለስ የአጭር ጊዜ ዕቅድ በማዘጋጅት ተግባራት መከናወናቸው ተጠቅሷል፡፡

ቀሪ ተግባራት የዎላይታ ብሔር የራሱ የሆነ ባህላዊ የዘመን አቆጣጠር በዉስጡ የሚይዛቸዉን ደቂቃዎችና ሰዓታትን፣ ቀናትን፣ ሳምንታትንና ወራትን እንዲሁም ወቅቶችን በትክክል የሚያሳይ በጽሁፍ የተቀመጠ መረጃ ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በቴክኒክ ኮሚቴ የቀረበዉ የአፈጻጸም ሪፖርት ሥራዉ ያለበት ደረጃ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ተገምግሞ በቀሪ ተግባራት ላይ በሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ቀጣይ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ተደርጓል።

በመድረኩ የፌደራል ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣ፣ የከልሉ ባህል ቱሪዝም ቢሮና የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የስራ ኃላፊዎች፣ የዞኑ አስተባባሪ እና የካቢኔ አባላት እንዲሁም የኖሚኔሽን ፋይል ዝግጅት ቡድን አባላት ተሳታች ሆነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *