
የ93 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው “ኦቶና” ሆስፒታል
ሆስፒታሉ ኤም አር አይ እና የመሳሰሉ የዘመኑን ህክምና ደረጃ የሚያሟሉ ቴክኖሎጂዎችንና ብቁ የሆኑ የህክምና ባለሙያዎችን በማሟላት የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ሆስፒታሉ የማከም፣ የመማር ማስተማር እና የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማዕከል የመሆን ዋና ዋና ዓላማዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሉቃስ ድንጋቶ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ 55 በላይ ስፔሻሊስትና ሳብ ስፔሻሊስት ሀክሞችንና 2336 የሀክሞችን አገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎችን በመያዝ ደቡብ ኢትዮጵያ ከ6 ዞኖችና ከ3 ክልሎች ለሚመጡ ከ15 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ሆስፒታሉ የመድሃኒት እጥረት ለመቅረፍ በየወሩ 700,000 ሺህ ብር በመመደብ ለእናቶችና ህጻናት ህክምና አገልግሎት የሚውሉ መድሀኒቶች እንዲገዛ ተወስኖ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተሩ ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በቀን 12 ሺህ ብር ተመድቦ ከሆስፒታሉ ውስጥ የማይገኙ መድሀኒቶች የመክፈል አቅምለሌላቸው ደሀ እናቶች ከግል መድሀኒት ቤት በስማቸው እንዲገዛላቸው እየተደረገ ይገኛል።
ከኢትዮጲያ የመድሀኒት አቅርቦት አገልግሎት የማይገኙ መድሀኒቶችን ከሶስት የጅምላ መድሀኒት አቅርቦት ጋር በጨረታ በማወዳደር የረጀም ጊዜ ውል በመግባት የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖርና እንዳይቆራረጥ እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የከፍተኛ ስፔሻሊስት ሀኪሞች የበሽተኞችን ጉብኝት በቀን ከሁለት ወደ አራት እንዲያድግ ተደርጎ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሳለጥ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ሆስፒታሉ ከ93 ዓመት ዓመት በፊት የተሰራው ህንጻ የዚህን ወቅት አገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን የማይመጥን በተለይም ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት መስጫ፣ የአጥንት ህክምና አገልግሎት መስጫ፣ የህጻናትና እናቶች ህክምና አገልግሎት መስጫ ክፍል እና ስፔሻሊቲ ተኝቶ ህክምና አገልግሎት ክፍሎች ምቹ ባለመሆናቸው በተገልጋዮች ዘንድ እሮሮ ሲያስነሳ መቆየቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ችግር ለመቅረፍ ከ10 ሚለዮን ብር በላይ በመመደብ ማስፋፊያ መሰራቱን ጠቅሰው የሰው ኃይል ከማደራጀት አንጻርም በዚህ ዓመት ብቻ 13 ስፔሻሊስት ሀኪሞችን ጨምሮ ከ600 በላይ አዳዲስ ሰራተኞችን መቅጠር መቻሉን ገልጸዋል።
ከእርግዝናና ወሊድ ጋር ተያይዞ ሊየጋጥሙ የሚችሉ ድንገተኛ የህክምና አገልግሎትን በሚመለከት ለሆስፒታሉ ማህበረስብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የተሰራ ሲሆን በተጨማሪም የማኔጅመንት አባላት የእናቶች ሀክምና የሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ክፍተተችን በመለየት የማስተካከያ በመወሰድ ወደ ሆስፒተሉ ሪፈራል የሚልኩ አጥቢያ ጤና ተቋማትን አቅም የማብቃትና የማጠናከርና ስራ እየተሰራ ሲሆን እያንዳንዱ ሪፈራል ላይ የጽሁፍ እና የቃል ግብረ መልስ እየተሰጠ ስለመሆኑ ዋና ዳይረክተሩ አብራርተዋል።
ከሆስፒታሉ ቆይታ ጋር ተያይዞ የመጣውንና መልካም የሆነውን የስራ ባህል መጠቀም የሚያስችል ምቹ ሁኔታ በመፍጠርና ዘመኑ የሚጠይቀውን የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የባለሙያዎች የተጨማሪ ትምህርት ፍላጎትን ያለገደብ በመስጠት በሆስፒታሉ የዓላማና የተግባር አንድነት የማስፈን ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር ሉቃስ አብራርተዋል።
ሆስፒታሉ በ2022 ዓ/ም የኩላሊትና የካንሰር ህክምና የሊህቀት ማዕከል ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የመድኃኒትና የህክምና ግብአት ችግር፣ በጤና መዲህንና በነጻ ህክምና አገልግሎት ክፊያ በወቅቱ አለመክፊል የባለሙያዎችን ትርፍ ሰዓት አገልግሎት ክፍያ ለመክፈል እንቅፋት መሆኑ እና ከቦታ እጥረት ጋር ተያይዞ በተለይም የቀዶ ጥገና ህክምና ቀጠሮ ረዥም መሆን ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰው ሆስፒታሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሰው ልጅ የውስጥ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎችን ለመመርመር የኤም. አር. አይ የተሰኘ መሳሪያ እጅግ የተወሳሰቡና ቀደም ሲል ለመለየት አስቸጋሪ የነበሩ በሽታዎችንና የሰውነት እክሎችን በመለየት የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያችል በሰማኒያ ሚሊዮን ብር ተገዝቶ ተግባራዊ መደረጉንም አብራርተዋል።

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ2022 የኩላሊትና የካንሰር ህክምና አገልግሎት የሊህቀት ማዕከል ለመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በፌዴራል ጤና ሚኒስቴር በተደረገ አጠቃላይ የአፈጻጸም ግምገማ ተፈላጊውን ሙያዊ ፥ ድርጅታዊ እና ሌሎች መስፈርቶችን ማሟላቱ ተረጋግጦ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት እንደተበረከተለት ይታወቃል።
