
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፖሊስን ዘመናዊ ሰራዊት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ብቃትና ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋገጡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ጉብኝት አድርገዋል።

ጉብኝታቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍም ፖሊስ እንደ ህግ አስከባሪ ህግ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ እንደ ወንጀል መርማሪ የወንጀል ምርመራ ክህሎት ያለው፣ የስነ-ባህሪ ጥናት ያጠና፣ የስነ ባህሪ ሳይኮሎጂን ጠንቅቆ የሚያውቅ ለማድረግ የተጀመረው ሪፎርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም እንደ ሰራዊት ወታደራዊ ብቃት ያለው፣ እንደ አድማ በታኝ የተሟላ ተክለሰውነት ያለው፣ እንደ ደህንነት ተቋም መረጃ መሰብሰብና መተንተን የሚችል፣ ዘመኑን ለመዋጀት ቴክኖሎጂ ብቃትና ግንዛቤ ያለው፣ ዐሻራ፣ ዲ.ኤን.ኤ. እና ዲጂታል ፊርማ እንዲሁም ዲጂታል ፎረንሲክ መተንተን የሚችል ዘመናዊ ሰራዊት እንዲሆን የተጀመረው ሪፎርም እንደሚቀጥልና መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንሚያደርግም አስታውቀዋል።