ደመናን የማበልፀግ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መደበኛ ዝናብ ባለማግኘታቸው በድርቅ የተጎዱት የቦረናና ኮንሶ አከባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ አገኙ። ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በአካባቢዎቹ ደመናን የማበልጸግ ስራ ተከናውኗል።ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፥ ደመና የማበልፀግ ስራውን ተከተሎም በሰሜን ምስራቅ ኮንሶና በደቡብ ወንጮ አከባቢ ከባድ ዝናብ ተመዝግቧል።በኮፈሌና ሻኪሶ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ሲጥል፥ በላንጋኖ ሀይቅ አከባቢ እና በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ ያቤሎ እንዲሁም በደቡብ ጉግዳ ቀለል ያለ ዝናብ ጥሏል።ደመናን የማበልፀግ ቴክኖሎጂ ደመናን ወደ ዝናብ ለመቀየር ከማስቻሉ በተጨማሪ ዝናብ በሚፈለግበት ቦታ እንዲዘንብ ያስችላል።እንደ ባለሙያዎች ማብራሪያ ደመናን ለማበልፀግ በመጀመሪያ በከባቢ አየር ውስጥ ለመበልፀግ በቂ የሆነ ደመና መኖሩን ማረጋገጥን ይጠይቃል።
