FB_IMG_1648562684754

የገዛ ወንድሙን 30 ሜትር ገደል ወስጥ ገፍትሮ በመክተት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገዉ ተከሳሽ በእስራት ተቀጣ

ወንድሙን 30 ሜትር ገደል ወስጥ ገፍትሮ በመክተት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገዉን ተከሳሽ በእስራት ማስቀጣቱን በቤንች ሸኮ ዞን የሼይ ቤንች ወረዳ ፖሊስ አስታወቀ።

የሼይ ቤንች ወረዳ ፖሊስ የታክቲክና ወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ ዋና ሳጅን ሙሉ አበበ እንደገለፁት ተከሳሽ ደምሴ ሶኪያ የእስራት ቅጣቱ ሊወሰንበት የቻለዉ በቤንች ሸኮ ዞን ሸይ ቤንች ወረዳ ባታ ቀበሌ ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት የገዛ ወንድሙን በዱላ በመደብደብና 30 ሜትር ገደል ዉስጥ ገፍትሮ ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዉን በቁጥጥር ስር በማድረግ ባደረገዉ ምርመራ ከግል ተበዳይ የሆነዉ ወንድሙ ጋር በነበረዉ ፀብ ምክንያት በአካባቢዉ ባህል መሠረት ጉዳያቸዉ በሽምግልና ታይቶ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ለታላቅ ወንድሙን እንዲክስ ብይን በሽማግሌዎች ይወሰንና ዉሳኔዉን ተቀብሎ እያለ ጥር 9 ቀን 2014 ዓ.ም ገበያ አምሽቶ እየተመለሰ ያለዉን መንገድ በመጠበቅ በያዘዉ ዱላ ከኋላዉ በመምታት መሬት ከጣለዉ በኋላ 30 ሜትር ገደል ዉስጥ ገፍትሮ ህይወቱ እንዲያልፍ ማድረጉን በምርመራ ማረጋገጡን አስረድተዋል።

ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በተከሳሽ የእምነት ቃልና በህክምና ማስረጃ አደራጅቶ ለዐቃቤ ህግ መላኩን ገልፀዋል።

የዞኑ ዐቃቤ ህግ ከፖሊስ የደረሰዉን መዝገብ ተንተርሶ ተከሳሽ ደምሴ ሶኪያን በቂም በቀል ተነሳስቶ በፈፀመዉ የወንጀል ድርጊት ግለሰቡን በግድያ ወንጀል ክስ መስርቶበት ፍርድ ቤት አቅርቦታል።

የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ሲያከራክር ቆይቶ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሲል ብይን ሰጥቷል።

በዚሁ መሠረት የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት መጋቢት 07 ቀን 2014 ዓ.ም ባስቻለዉ የወንጀል ችሎት ተከሳሽ ደምሴ ሶኪያ በ12 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።