

የእንሰት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት እና የእንሰት ሰብል ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ አስተውቀዋል።

የአፕላይድ ሳይንስ ዩንቨርሲቲ የሆነው ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው መስክ የልህቀት ማዕከል ለመሆን አልሞ ዘርፈ ብዙ የጥናትና ምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ከነዚህ ዘርፎች አንዱም የእንሰት ሰብል ምርት ተጠቃሽ ነው።
እንሰት ለዎላይታ እና ለአከባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርምር፤ የማህበረሰብ አገልግሎት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን በስፋት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ነው በዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በእንሰት ላይ አንጋፋ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ቦሻ ያሳወቁት።
እንሰት በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙት ዋና ዋና ሰብሎች አንዱ መሆኑንና ከ10,000 ዓመታት በፊት እንደተጀመረ ታሪክን መረጃን በመጥቀስ ዶ/ር አብርሃም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች እንሰት በዋናነት የሚታወቅ ሰብል መሆኑን ዶ/ር አብርሃም ጠቁመው፤ በእነዚህ አከባቢ ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብሉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይሰጣል ብለዋል።

እንሰት በኢትዮጵያ ከባህር ጠለል በላይ ከ1500 – 3100 ሜ ባሉት ከፍታ እና 900 ሚ.ሜ አማካይ የዓመት ዝናብ መጠን ያላቸዉ ቦታዎች ተስማሚ እንደሆነ ነው ተራማሪው የገለጹት።
እንደ ተማራማሪው ገለጻ፤ በአሁኑ ሰዓት እንሰት ዝናብን የምተካ አማራጭ የውሃ ምንጮች ባሉበት አከባቢ ከ1500 ሜ በታች በሆኑ ቆላማ አካባብዎችም ሊመረት ችላል።
እንሰት በባህሪዉ ለም አፈር የሚፈልግ እንደሆነና እንክብካቤ ከተደረገለት በብዙ የአፈር ዓይነቶች ላይ ይበቅላል ያሉት ዶ/ር አብርሃም፤ እንሰት የሚመረትበት አካባቢዎች ከፍተኛ የሕዝብ ብዛትና ጥግግት ያላቸው እንደሆነም አውስተዋል።
እንሰት ከጥቂት እርሻ ማሳ ብዙ ምርት በመስጠቱ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ጠቀሜታዉ የጎላ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አብርሃም፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ 20 በመቶ የሚበልጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች እንሰትን ለምግብነት እንደሚጠቀሙ
ይገመታል ሲሉም ጠቁመዋል።
የዎላይታ ዞን እንሰት አብቃይ ከሆኑት የደቡብ ኢትዮጵያ ዞኖች አንዱ እንደሆነ የገለጹት ተመራማሪው፤ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአደገኛ ሁኔታ ምርቱና ምርታማነቱ ከመቀነዱም ባሻገር ወደ መጥፋት ደረጃ እየደረሰ መሆኑን አብራርተዋል።
የእንሰት ምርትና ምርታማነት እየቀነሰ ስለመምጣቱ በሳይንሳዊ ትንተና ብዙ ምክንያቶችን መስጠት የሚቻል መሆኑን የገለጹት ተመራማሪው ወደ መፍትሄው በአፋጣኝ ካልተከደ ግን ጉዳቱ እየጨመረ ሄዶ ወደ ማይመለስበት መድረሱ አይቀረ ነውም ብለዋል።
በዎላይታ ዞን ካሉት ወረዳዎች በባይራ ኮይሻ፣ ቦሎሶ ሶሬ እና ሶዶ ዙሪያ ወረዳዎች በጥቅት አርሶአደሮች በተደረገ አጭር የዳሰሳ ጥናት የተገኘው ውጤት በጥቅሉ በእንሰት
ላይ ትልቅ አደጋ እንደተጋረጠ መሆኑን ዶ/ር አብርሃም አብራርተዋል።
እንደ ዩንቨርሲቲው ኮሙኒኬሽን ዘገባ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን የሚሰጠውን የእንሰት ሰብልን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል ጥምር ግብረ-ኃይል በማቋቋም ዘላቂነት መፍትሄን በማበጀት ዘላቂ መፍትሄን ማበጀት ቅድምያ ሊሰጠው ይገባል ሲሉም ተመራማሪው አሳስበዋል።
