
ብሩክ በቀለ ይባላል በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለምዶ ፋና የእህል ጎተራ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው ተወልዶ ያደገው፡፡ የፈጠራ ባለቤት የሆነው ወጣት በልጅነቱ የሽቦ መኪና በመገጣጠም፣ የተበላሹ የሕፃናት መጫወቻዎችን ዳግም እንዲሰሩ በማድረግ ዛሬ ላይ የደረሰበትን ፈጠራ እውንነቱን ለማረጋገጥ ፍንጭ እንደነበሩ ወጣቱ ይናገራል፡፡

ወጣት ብሩክ ዕድሜው አሁን 26 ዓመቱ ሲሆን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ የ2011 ዓ.ም ምሩቅ ነው፡፡
ትናንሽ የሚመስሉ የፈጠራ ስራዎችን ቤት ውስጥ ከመሞከር ባለፈ በትክክል ስራዎችን መስራት የሚችልበት አጋጣሚ የተፈጠረለት 7ኛ ክፍል ላይ ነበር፡፡ ወጣት ብሩክ ከደሬቴድ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለፀው፤ መምህራቸው ፕሮጀክት ሰርተው እንዲያመጡ በተሰጣቸው የቤት ስራ አማካኝነት ሲሆን በ1 ሰዓት ውስጥ 3 ሺህ ሜትር የሚጓዝ፣ 6 ፉርጎ ያለው፣ 120 ሜትር ርዝመት ያለው፣ የሆነና ያለሀዲድ መሬት ላይ መሄድ የሚችል ተንቀሳቃሽ ኃይል የሚሞላ ባቡር ሰርቶ ማቅረብ እንደቻለና በሰዓቱ የሰራው ባቡር ሲንቀሳቀስ ሲያይ የነበረውን ደስታ እስከዛሬ እንደማይረሳው ያስታውሳል፡፡

የፈጠራ ባለሙያው ወጣት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትምህርት ቤታቸውን በመወከል የተለያዩ ስራዎችን በመስራት የማበረታቻ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡
በአሁኑ ሰዓትም ወጣት ብሩክ በቀለ EW-13 ላይት ኤር ክራፍት አውሮፕላን ሰርቶ ለመጨረስ 20 በመቶ የቀረው ሲሆን ለዚህም ስራ የሚመለከታቸው አካላት ዕውቅና ሰጥተውታል፡፡
አዲሱ EW አውሮፕላን ተሰርቶ ሲጠናቀቅ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ከሰዎች ቁጥጥር ውጪ የሚሆኑ የእሳት አደጋ ሲከሰት ለማጥፋት፣ ለካርታ ስራዎች፣ የአንበጣ መንጋ ሲከሰት መድሃኒት ለመርጨትና ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል እንደሆነም አስረድቷል፡፡
የፈጠራ ስራውን ለመስራት ያነሳሳውን አጋጣሚም በባሌ ብሔራዊ ፓርክ እሳት አደጋ በተከሰተበት ወቅት ከደቡብ አፍሪካና ከተለያዩ ሀገራት በኪራይ አውሮፕላን ተፈልጎ እስኪመጣ እሳቱ ያስከተለውን አደጋ በተመለከተ ወቅት የመስራት ፍላጎት አሳደረበትና ብሰራው ያሉት ችግሮችን ሊቀረፉ ይችላሉ የሚለውን ሀሳቡን ወደ ፈጠራ ለመቀየር መወሰኑን ይገልፃል፡፡
በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም እየተማረ በትርፍ ሰዓቱ ዲሽ በመገጣጠም፣ የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ስራዎችን በመስራት እንዲሁም ቤተሰቦቹንና አንዳንድ የዲያስፖራ ወዳጆቹ በሚልኩለት ገንዘብ ለአውሮፕላን ስራ የሚያስፈልጉትን እቃዎች በመግዛት ትምህርቱን ጨርሶ ሲመለስ በ2013 ዓ.ም አቅዶት የነበረውን አውሮፕላን ለመስራት ችሏል፡፡
አሁን ስራው ወደ 80 በመቶ የደረሰ ሲሆን አውሮፕላኑ ከመብረሩ በፊት መንደርደር ወይም የመሮጥ ደረጃ ደርሶ መብረር እንደሚቀረው የሚገልፀው ወጣቱ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብሲኒያ ፍላይት አካዳሚ ለማብረር የሚያስችሉትን ዋና ዋና የሚባሉ ስልጠናዎችን እንደወሰደ ተናግሯል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አውሮፕላኑ የሴፍቴ ማቴሪያሎች ባለመሟላታቸው ማብረር እንዳልቻለና እቃዎቹን ለማሟላት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን አቅሙ ስለማይፈቅድ ለሚሟላት ስፖንሰር የሚያደርገው አካላት እየፈለገ እንደሆነ ተናግሯል፡፡
ከፌዴራል የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መጥተው ስራውን እንደተመለከቱ እና ከዞኑ አስተዳደር ጋር ተነጋግረው የመስሪያ ቦታ እንደሚያመቻች ቃል የተገባለት ቢሆንም በየጊዜው ባለመፈፀሙ ምክንያት ባለስልጣናት በሚቀየሩበት ወቅት ጉዳዩን እንደ አዲስ በመመልከት ቃል የተገባውን የመስሪያ ቦታ ባለመሰጠቱ መቸገሩን አንስቷል፡፡
ለሀገር የሚጠቅም ስራ ቢሰራም የፈጠራ ስራዎቹን ማስቀመጫ ቦታ በማጣት ሰው ጊቢ ውስጥ ስላስቀመጠ በየጊዜው ስራዎቹን እያሻሻለ መስራት እንዳልቻለ ተናግሯል፡፡

እኛም ወጣት ብሩክን ለማግኘት በሄድንበት ወቅት አውሮፕላኗ በሸራ ተሸፍና ፀሐይና ዝናብ እንደተፈራረቀባት ሲሆን ወጣቱ በዚህ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን ከዚህም ሌላ በኮቪድ ወቅት የኬሚካል መርጫ ማሽን ሰርቶ እንደነበርና የሚደግፈውን አካል ባለማግኘቱ ምክንያት እንዳስቀመጠው አንስቷል ስል ደሬቴድ ዘግቧል፡፡