FB_IMG_1648958606470

አቶ እንግዳወርቅ ዳንኤል ነዋሪነታቸው በዎላይታ ዞን አረካ ከተማ ሲሆኑ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው።

አቶ እንግዳወርቅ በአረካ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት በቋሚ የመንግስት ሥራ ተቀጥረው እያገለገሉም ይገኛሉ።

ከሥራ ሰዓት ውጪ ያሉ ትርፍ ጊዜያትን ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ በኩር ልጃቸውን፣ ባለቤታቸውንና ሌሎች ሠራተኞችን በቀን ሥራ በማሰማራት በመኖሪያ ቤታቸው ሳሙና በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ።

የሳሙና ስያሜውም “እንቻቻል”የሚል እና እስከ 300 ግራም የሚመዘን ሲሆን በዝቅተኛ ዋጋ ከ13 ብር እስከ 15 ብር እየተሸጠ ይገኛል።

ሞራ እና የፋብሪካ ኬሚካሎች ለምርቱ የሚያገለግሉ ግብዓቶች ስለመሆናቸው በመኖሪያ ቤታቸው በተገኘን ጊዜ ማየት ችለናል።

ባልና ሚስት አብረው ተደጋግፈው እና አንዱ ሌላውን ተክቶ በመስራት ዛሬ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከፍ ማድረግ ችለዋል።

ወይዘሮ ተዋበች ታደሰ የአቶ እንግዳወርቅ ዳንኤል ባለቤት፤ ለሳሙና ምርት ሞራን መቀቀል እና ሌሎች የቤተሰብ ኃላፊነቶችንም በአግባቡ በመወጣት አባወራው በማይኖርበት ጊዜ ሥራውን ያሰራሉ፣ ያሰራሉ። ልጆቻቸው እንደሚረዷቸውም ይናገራሉ፡፡

ወይዘሮ ሽታዬ ፅጉ እና አቶ ዳርጌ ኡልሶ የሥራ ዕድል ያገኙ ሰራተኞች ናቸው። ስለሆነም በዚህ ሥራ በቀን በሚከፈልላቸው ገንዘብ ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድራሉ።

ወ/ሪት ሀና አሸቦ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማራች ወጣት ስትሆን፣ይህ የፈጠራ ስራ ያስገኘውን የሳሙና ምርት በ13 ብር በመግዛት ለሸማቹ ህብረተሰብ ደግሞ በችርቻሮ ዋጋ በ17 ብር በመሸጥ ትርፍ እያስገኘላት እንደሆነ ተናግራለች።

የዚህ ሳሙና ምርት ተረካቢ ደምበኛ ወይዘሮ ታደለች አይድቆ ሸማቹ ምርቱን እንደወደደ እና የመግዛት ፍላጎት እየጨመረ እንደሆነ ገልፃለች።

የምርቱ ባለቤት የሆኑት አቶ እንግዳወርቅ ዳንኤል ግን ምርቱን በብዛትና ጥራት ለማምረት ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም የማምረቻ ቦታ ጥበትና የመሸጫ ቦታ ችግሮች ቢፈቱ የተሻለ ምርት ለገበያ ለማቅረብ ዓለማ እንዳላቸው ተናግረዋል።

“ዛሬ ላይ ብዙ የሥራ አጥነት ችግር እየተስተዋለ ባለበት ጊዜ እንዲህ አይነት የፈጠራ ባለቤቶች አስተማሪዎቻችን ስለሆኑ ሥራዎቻቸውን ለሌሎች የሚያሳዩበትንና የሚሸጡበትን ቦታ የመስጠትና የማቀናጀት ሥራ ከእኛ ስለሚጠበቅ በዚህ ጉዳይ ላይ የከተማ አስተዳደሩ አበክሮ ይሰራል” ያሉት ደግሞ የአረካ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና እንተርፕራይዞችና እንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ እያሱ ጩብሶ ናቸው ሲል ደሬቴ ዘግቧል።