

በደቡብ ክልል በተለያዩ ተቋማት ከደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈለ ከ343 ሚሊዮን ብር በላይ በሂሳብ ምርመራ መገኘቱ ተገልጿል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ፋይናንስ መምሪያ የተቋሙን የስድስት ወራት አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል።
በዚህ ወቅት የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምህረቱ አሰፋ፤ በክልሉ የመንግስት ሀብትና ንብረት የሚመሩባቸው ደንቦችንና መመሪያዎችን በአግባቡ መተግበር ላይ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ተናገረዋል።
በክልሉ የተለያዩ መንግስታዊ መዋቅሮች ለሌብነትና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ችግሩን በመፍታት ሀብቱን ለሚፈለገው ልማት ለማዋል አመራሩ መስራት አለበት ብለዋል።
በክልሉ ከ2013 ጀምሮ ተለያዩ ተቋማት በተደረጉ የሂሳብ ምርመራዎች ከደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈለ ከ343 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ገልጸው፤ይህ ከፍተት ከታየባቸውም የግንባታ ዕቃዎች ግዥ፣ የአበል አከፋፈልና ጨረታ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ያለአግባብ ከተከፈለው ከዚሁ ገንዘብ ውስጥ 141 ሚሊዮን ብር ወደ መንግስት ከዝና እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ አቶ ምናሴ ዘውዴ በበኩላቸው፤ወስን የመንግስትና ህዝብ ሀብት በተቀናጀ መልኩ ለልማት ለማዋል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በግማሽ የበጀት ዓመቱ ውስጥ በተቋማት በተደረገ የኦዲት ግኝት ከደንብና መመሪያ ውጪ ሊባክን የነበረ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
አቶ ምናሴ፤ ከመመሪያ ውጪ በመስራት እጃቸው ያለበትን አካላትን ለህግ የማቅረብ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የኦዲት ግብረ ሀይል አስመላሽ ኮሚቴ በማቋቋም የመንግስትና የህዝብ ሀብቶች እንዳይባክኑ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ምክር ቤት የኢኮኖሚ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወግነሽ ፊንሳ ናቸው።
ሀብትን የሚያባክኑ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል ህጋዊ አሰራር ተፈጻሚ እንዲሆን ምክር ቤቱ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የመንግስትና የህዝብ ሀብት ካለብክነት ተጠብቀው ለልማት በማዋል በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎች ምክንያት እየተፈጠረ ያለውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የውስጥ ገቢን ማሳደግ ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን መከተልና ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ እንደሚገባም ተመላክቷል።