የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በዎላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ የቡጌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያስገነባውን ፕሮጄክት ርክክብ አደረገ።

በትምህርት ቤቱ የተገነባው ባለ አንድ ብሎክ አራት መማሪያ ክፍሎች በሁለት ፈረቃ 480 ተማሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችልም ተጠቁሟል።

ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ላይ ተሞርኩዞ በርካታ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን በመተግበር የህዝብ አለኝታነቱን ማስመስከር ችሏል።

ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ በተከታታይነት ተግባራዊ ካደረጋቸው የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች መካከል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በትምህርት ቤት ግንባታና ግብዓት አቅርቦት ተጠቃሽ ነው።

በዛሬው ዕለትም የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ እና በዘርፉ የሚገኙ የተለያዩ ዳይሬክተሮች እና ፕሮጀክቱን የሚተገብረው የስነ ትምህርትና ባሕሪ ጥናት ኮሌጅ አባላት በተገኙበት ዩኒቨርሲቲው በዎላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ቡጌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት ያስገነባውን ትምህርት ቤት ርክክብ ተደርጓል።

ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ችግር በጥናትና ምርምር በመለየት የቅድምያ ቅድምያ ሰጥቶ ከሚተገብራቸው አበይት የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች የትምህርት ቤት ግንባታና ግብዓት አቅርቦት ዋንኛው ነው ብለዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ በዎላይታና አካባቢው ላይ በትምህርት ጥራት ላይ አዎንታዊ እምርታ ለማስመዝገብ ዩኒቨርሲቲው እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንና በተለይም ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና አስፈላጊውን የትምህርት ግብዓት በማቅረብ ረገድ ጅምር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም ገልጸዋል።

በዎላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ቡጌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት የተገነባው ባለ አንድ ብሎት አራት የመማሪያ ክፍሎች በቀጣይ ጊዜያት በወንበር ጠረጴዛ፣ በመጽሐፍት፣ በላቦራቶሪ ቁሳቁሶች የተሟሉ እንዲሁ ይሰራል ሲሉም ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

ትምህርት ቤቱን ሞዴል ማድረግ ግባችን ነው ያሉት ዶ/ር መስፍን፤ ለሀገሪቱ ብቁ የሰው ኃይል ልማት ላይ የድርሻችንን ለመጣት አበክረን እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።

በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዳዊት ዳልጋ በበኩላቸው በዳሞት ጋሌ ወረዳ ቡጌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተገነባው ይህ ትምህርት ቤት ለተማሪዎች የተሟላ ለውጥ ለማምጣት አስቻይ ነው ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በትምህርት ልማት ላይ የጀመረው መጠነ ሰፊ ስራ በትምህርት ጥራት ላይ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ መልካም ዕድል ይፈጥራል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክት የትምህርት ማስፋፊያ ተግባር በእቅድ ተይዞ በቀጣይም ተጠናክሮ በሌሎች አካባቢዎች ይቀጥላል ብለዋል ዶ/ር ዳዊት ዳልጋ።

በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ስነ-ትምህርትና ባሕሪ ጥናት ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር መብራቱ በለጠ በበኩላቸው የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ አስቀድሞ የመማሪያ አካባቢን ምቹ ማድረግ ግድ እንደሚል ገልጸው፤ በኮሌጁ መምህራን የተያዙ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶች በቀጣይ ጊዜያትም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ብለዋል።

በኮሌጁ ምክትል ዲን የሆኑት ዶ/ር እንዳለ ብርሃኑ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ይህንን መሰል ተግባራት ተጠናክሮ መቀጠል  እንዳለባቸው ገልጸው፤ ሀብት በማፈላለግ መሰል ችግር ፈቺ የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት እንዲጠናከሩ በባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ ትስስር መፍጠር ተገቢ ነው ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ የሆኑት መምህር መስፍን በልጉ በበኩላቸው ይህ ፕሮጀክት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ታስቦ እንደተጀመረ ገልጸው፤ በአንድ መማሪያ ክፍል ውስጥ ውስን ተማሪዎች እንዲማሩ በማስቻል ከዚህ ቀደም የነበረውን የክፍል እጥረት ይቀርፋል ብለዋል።

በቀጣይም የላይብረሪ እና ላቦራቶሪ ግብዓቶችን ለትምህርት ቤቱ ለማበርከት እቅድ መያዙን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አውስተዋል።

የቡጌ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ወርቁ ካሳ በበኩላቸው፤በትምህርት ቤቱ ዛሬ ላይ 810 ተማሪዎች እስከ 11 ክፍል ድረስ እያስተማሩ እንደሚገኝ ተናግረው፤ የፕሮጀክቱ መተግበር ከዚህ ቀደም የነበረውን የክፍል ጥበት ችግር እንደሚቀርፍ ብሎም በቀጣይ 12ኛ ክፍል ትምህርት ለማስጀመር ላይሰንስ ለማውጣት አጋዥ ነው ብለዋል።

ርዕሰ መምህሩ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ላበረከተው ከፍተኛ ትብብር አመስግነው፤ ቀጣይ ላብሬሪና ላቦራቶሪ ለማደራጀት እንድንችል ድጋፋችሁ አይለየን ብለዋል።

በትምህርት ቤቱ የተገነባው ባለ አንድ ብሎክ አራት መማሪያ ክፍሎች በሁለት ፈረቃ 480 ተማሪዎችን ማስተናገድ እንደሚችልም ተጠቁሟል ሲል የዩንቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬት ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: