ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በግል ባንክ ያላቸውን አካውንት ዘግተው ማስረጃ ካላቀረቡ በጀታቸውን ማንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን ጭምር አስታውቋል፡፡

የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ የግል ባንኮች የከፈቷቸውን ሒሳቦች በአስቸኳይ እንዲዘጉ፣ይህንንም ማድረጋቸውን የሚያረጋግጥ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ታታዙ፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር በግል ባንኮች ውስጥ አካውንት ከፍተው ገንዘብ እያንቀሳቀሱ ነው ለተባሉ መሥሪያ ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ፣ በግል ባንኮች ውስጥ ያላቸውን ሒሳብ ካልዘጉ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስጠንቅቋል፡፡

በገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) የተጻፈው ይኼው ደብዳቤ፣ በመንግሥት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ መሠረት፣ የመንግሥት ገንዘብ ወይም ገቢ የሚደረገው በብሔራዊ ባንክ ወይም ብሔራዊ ባንክ በሚወክለው ባንክ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለጊዜው የሰየመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ብቻ መሆኑን የሚኒስትር ዴኤታው ደብዳቤ ያመለክታል፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በርካታ የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት ገንዘብ ለማንቀሳቀስ በግል ባንኮች ሒሳብ በመክፈት ላይ መሆናቸውንና ይህንን ማቋረጥ እንደሚኖርባቸው በመታመኑ ዕርምጃው እንደተወሰደ ታውቋል፡፡

በመሆኑም ይህንን ተግባር የፈጸሙ፣ እንዲሁም በዚህ በሒደት ላይ የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የከፈቱትን የባንክ ሒሳብ በመዝጋት ለገንዘብ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያደርጉም አሳስቧቸዋል፡፡

መሥሪያ ቤቶቹ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን በሚደረገው ማጣራት፣ በግል ባንኮች ውስጥ የተከፈተ የባንክ የሒሳብ ቁጥር ከተገኘባቸው፣ ዕርምጃ እንደሚወስድባቸውም የሚኒስትር ዴኤታው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር እወስደዋለሁ ካለው ዕርምጃ ባሻገር፣ እነዚህ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች በግል ባንክ ያላቸውን አካውንት ዘግተው ማስረጃ ካላቀረቡ በጀታቸውን ማንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን ጭምር አስታውቋል፡፡

ይህንን ትዕዛዝ ለማስፈጸም የገንዘብ ሚኒስቴር የትሬዠሪ ዳይሬክቶሬት ትዕዛዝ እንደተሰጠውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሚኒስትር ዴኤታው ደብዳቤም ይህንን በተመለከተ፣ ‹‹የመሥሪያ ቤቶችን ትሬዠሪ ዳይሬክቶሬትም የባንክ ሒሳብ ቁጥር የከፈቱ ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የሒሳብ ቁጥሩን ዘግተው ማስረጃ ካላቀረቡ፣ ምንም ዓይነት ገንዘብ እንዳይተላለፍላቸው፣ እንዲሁም የኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬትም በውስጥ ኦዲት በኩል ክትትል አድርጎ ሪፖርት እንዲያቀርብ ታዟል፤›› ይላል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞኑን ያስተላለፈው ይህ ትዕዛዝ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግል ባንኮች የተከፈቱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አካውንቶች እንዳያንቀሳቀሱ የሚያደርግ ሲሆን፣ ገንዘባቸውን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲያስተላልፉ እንደሚያስገድድ ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የግል ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች አስረድተዋል፡፡

በዚህ ዕርምጃ ላይ ቅሬታ ያላቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የግል ባንክ ኃላፊዎች፣ መንግሥት የሕዝብ ገንዘብ መንቀሳቀስ ያለበት በአንድ ባንክ ብቻ እንዲሆን መወሰኑ ተገቢ አለመሆኑንና በፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን የውድድር መንፈስ የሚያጠፋ ነው ብለውታል፡፡

በአንድ በኩል የውጭ ባንኮች ይግቡ እየተባለና መንግሥትም አገር በቀል ባንኮችን አበረታታለሁ ብሎ እየተናገረ፣ በተግባር ግን እንዲህ ያለውን ዕርምጃ መውሰዱ ግራ ያጋባል በማለት ዕርምጃው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ካሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሒሳባቸውን ከንግድ ባንክ ወደ  ተለያዩ የግል ባንኮች የሚያዘዋውሩ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱ እየተነገረ ሲሆን፣ መንግሥት አሁን የወሰደው ዕርምጃ ከዚህ ጋር ተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡

አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች አካውንታቸውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ግል ባንኮች ሲያዛውሩ ለሠራተኞቻቸው ብድር ለማመቻቸት የተደረጉ ስምምነቶችን ታሳቢ በማድረግ ጭምር እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን፣ እንዲህ ያሉ ስምምነቶች ያሏቸው መሥሪያ ቤቶችም እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል ሲል ሪፖርተር ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: