
የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በጥር 1/2013 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የቀድሞ የፓርቲውን ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረናን ከፓርቲው ሊቀመንበርነት አንስቶ አቶ ጎበዜ ጎአን የፓርቲው ሊቀመንበር በማድረግ አዲስ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አደራጅቶ በወጣትና በነባር አመራሮች የዎላይታ ህዝብ መፃኢ እድል ላይ በአሉታዊነት የሚቃጣን ኃይል ለመታገል ለዎላይታ ህዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን ለዎላይታ ህዝብ ነፃነትና እኩልነት እንዲሁም የራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ መብቱ እንዲረጋገጥ እየታገለና እያታገለ የሚገኝ የዎላይታ ህዝብ ፓርቲ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

ይሁንና በፓርቲው ስም ለዘመናት ሲነግድ የቆየውና እኔ ከፓርቲው ሊቀመንበርነት ከወረድኩ ፓርቲውን እበትናለሁ በማለት ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውጭ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቀድሞ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና ከድርጊቱ እንድታቀብ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም እምቢ አሻፈረኝ በማለቱ የፓርቲው ማዕከላዊ ምክርቤት ከየትኛውም ፓርቲን በሚወክሉ ጉዳዮች ላይ እንዳይሳተፍ፣ በፓርቲው ስም ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳይሰጥ፣ የፓርቲውን ስም ተጠቅሞ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በማገድ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ አሳውቋል።
ስለሆነም ከትናንት ጀምሮ አንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች ትስስር ገጾች አቶ ተክሌ ቦረና ሀገራዊ ምክክሩን አስመልክተው በፓርቲው ስም መግለጫ መስጠቱን በፊት ገጾቻቸው ይዞ በመውጣታቸው የዎህዴግ ሥራ አስፈጻሚ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የሚከተለውን አቋም ለህዝብ ይፋ አድርጓል።
1. በአቶ ተክሌ ቦረና ተሰጠ የተባለው መግለጫ የግለሰቡ እንጂ ፓርቲውን የማይወክል መሆኑን፣
2.የዎህዴግ ሥራ አስፈፃሚ ከሀገራዊ ምክክር ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ውይይት ያላደረገና በምክክሩ ዙሪያ አቋሙን ያላሳወቀ መሆኑን፣
በመግለጽ ለመላው አባላቶችና ደጋፊዎች እንዲሁም ለመላው ዎላይታ ህዝብ ከእንደዚህ ዓይነት ለግል ጥቅማቸው ብሎ የህዝብን ጥቅም ወደጎን በመተው ህዝቡን ከሚያደናግሩ ሰዎች ራሳችሁን እንድትጠብቁና ህገወጥነትን አጥብቃችሁ እንድትቃወሙ ዎህዴግ ሥራ አስፈፃሚ ያሳስባል።
መጋቢት 25/2014 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ፣ ኢትዮጵያ