የዎላይታ ቡና በራሱ ስምና ብራንድ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበትን ዕድል ስላገኘ የግብይት መጠኑን ከፍ ለማድረግ ዕድል መፍጠሩን የዎላይታ ገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ሥራ ዩኒየን ገለፀ።

ለዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ጥራቱን የጠበቀ የዎላይታ ቡና ለማቅረብ የሁለ-ገብ መሠረታዊ ኅብረት ስራ ማህበራት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ዳሞታ የዎላይታ ገበሬዎች ሁለገብ ህብረት ሥራ ዩኒየን የቡና ግዥና ወጪ እና የቡና ኤክስፖርት ከማሳ እስከ ግብይት ድረስ ያለውን ጥራት ችግር ቀጣይ ለመቅረፍ ከማህበራት የተውጣጡ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

የዎላይታ ዞን ኅብረት ስራ ጽ/ቤት ወ/ሮ ሰላማዊት ሳሙኤል ለማህበራት ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ መምሪያው ከዩኒየኑ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ጥራቱን ጠብቆ የተሰበሰበ ቡና በዓለም ገበያ የተሻለ ዋጋ እንደሚከፈልለት የጠቆሙት ወ/ሮ ሰላማዊት ለዚህም ማህበራት በደንብ አቅደው መስራት እንዳለባቸውና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

በቀጣይ በቡና ግብይት ውስጥ ያሉ ማነቆዎች ተፈተው ለቡና ጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

አቶ ዳሳና ዋና የዳሞታ ዎላይታ ገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ እንዳሉት ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለዓለም ገበያ በመላክ የዩኒየኑ ዕድገትንና ገቢን ለማሳደግ እንችላለን ብለዋል፡፡ 

የዎላይታ ቡና ከዚህ በፊት “የሲዳማ C” በሚል ስም ሲላክ እንደነበረ የገለጹት አቶ ዳሰና አሁን የዎላይታ ቡና በራሱ ስምና ብራንድ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበትን ዕድል ስላገኘ የግብይት መጠኑን ከፍ ለማድረግ ዕድል እንደፈጠረም አስገንዝበዋል፡፡

ዘንድሮ የዳሞታ ዎላይታ ገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒየኑ 8 ኮንቴይነር ቡና ምርት ለዓለም ገበያ ማቅረቡንም አስታውቀዋል፡፡

አያይዘውም ዘንድሮ 10 የቡና አምራች ማህበራት spp እና organic ሰርተፍኬት ማግኘታቸውን ስራ አስኪያጁ ጠቅሰው በዚህም የአንጩቾ ማህበር በጥራቱና በመጠኑ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቡንም አስታውቀዋል፡፡ 

የዳሞታ ዎላይታ ገበሬዎች ኅብረት ስራ ዩኒየን ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደምሴ ዳና በበኩላቸው የተሻለ ውጤት ለማምጣትና ትርፍን ለማግኘት ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የሁለ-ገብ መሠረታዊ ኅብረት ስራ ማህበራት አመራሮችና ሌሎች ባላድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: