

“ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት በተለያዩ ጊዜያት ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን በተለይም የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬሄሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በማተኮር መሰረት የሌላቸው የሀሰት መረጃዎችን በማጠናቀር ተቋምን የማጠልሸት፣ በጎ ገጽታን የመሸርሸር፣ ብሎም ተገልጋዩን ሕብረተሰብ በተቋሙ ላይ አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ ተከታታይነት ያለው ዘገባ ሲሰራ ቆይቷል” በማለት ዩንቨርስቲው ባወጣው መግለጫ አትተዋል።
“ይህ ግለሰብ የጋዜጠኝነት የሙያ ስነ-ምግባርን በመጣስ ከአገልግሎት ሰጪ ተቋም እና ከተገልጋልዩ ሕብረተሰብ በቂ እና ተገቢነት ያለውን መረጃ ሳያሰባስብ፤ ከአንድ ወገን ብቻ መረጃ እንደተቀበለ አድርጎ «የሀሰት መረጃን በማሰራጨት» ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን ለመኮነን እና ለማስኮነን የሄደበት ርቀት ለተቋሙ እና ለአካባቢው ሕብረተሰብ ያለውን የተዛባ አመለካከት እና ጥላቻ በተጨባጭ ያረጋግጣል” ብሏል።
ሚዛናዊ ዘገባን በመስራት ተገልጋይን ከአገልጋዩ ጋር ማቀራረብ፤ ችግሮች ካሉም ችግሮች የሚፈቱበትን አቅጣጫ በቂ መረጃ አሰባስቦ ማመላከት ከአንድ የበቃ ጋዜጠኛ የሚጠበቅ ሆኖ ሳለ፤ ይህ ግለሰብ ግን በስልክ እና በፌስ ቡክ የመልዕክት ሳጥን የሚላክለትን «ያልተረጋገጠና ያልተጣራ መረጃ» እንደ ወረደ ወስዶ ሐላፊነት በጎደለው ስሜት በመዘገብ ሙያው የሚጠይቀውን የስነ ምግባር መርህ እየጣሰ ይገኛል።
“ሀገር እንደ ሀገር በፈተና ውስጥ ባለች ወቅት እንኳ ሳይቀር ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት ሀገር አፍራሽ ተልዕኮ አንግቦ እንደሚንቀሳቀስ፤ ከመቀራረብ ይልቅ የሚለያዩ ሀሳቦሽን በመንዛት ጭምር ሰላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን በብዙ መልኩ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ፤ ህግ ባለበት ሀገር የሀሰት መረጃን በማሰራጨት ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ መሳተፉና ስርዓት አለመያዙ እየታወቀ አደብ የሚያሲዘው መጥፋቱ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ ተቋማትን ለጥያቄ ዳርጓል” ስልም መግለጫው ጠቅሷል።
“ይህ ግለሰብ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ ተቋማትን ሲዘልፍና ሲያንቋሽሽ፤ ያልተጣራ፥ ተሃማኒነት የሌለው ሀሰተኛ መረጃን በማሰራጨት የተቋም ገጽታን ሲሸረሽር፥ የተቋም አመራሮችን ሲዘልፍ፤ እውነት ሃይ ባይ ያጣው ግለሰቡ ከሕግ በላይ ሆኖ ነው!? ከተጠያቂነት ነጻ የወጣ ሆኖ ነው!? የሚያስብል ጥያቄን ያጭራል። ይህ ግለሰብ ከሚዛናዊነት እሳቦት ያፈነገጠ፥ የሚያሰራጨውም መረጃ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይንነት የለውም የምንለው በምክንያት ነው” ብሎ ቀጣዩን መግለጫ ለሚዲያችን በላከው መረጃ ልኳል።
1.” ለአብነት ያህል በ11/04/2014 ዓ.ም ከህክምና ስነ ምግባር፥ ደንብና ስርዓት ውጪ «የታካሚ ካርድ ሚስጢራዊነትን» በመጣስ ከህክምና ባለሙያው ፍቃድ ውጪ ለማንም መተላለፍ የሌለበትን የታካሚን ካርድ የሀሰት ወሬ ከሚያቀብሉት ግለሰቦች ፎቶ ተነስቶ የተላከለትን ካርድ ፌስ ቡክ ገጹ ላይ መለጠፉ እና የጋዜጠኝነት የሙያ ስነምግባር ከሚፈቅደው ውጭ ሚዛናዊነት የጎደለውን ዘገባ ሰርቶ ማሰራጨቱ”።
2. “የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጉዳዩን እንዳጣራ እና በሆስፒታሉ የተከሰተው ችግር እውነት መሆኑን አውቆ መቀበሉን እንዲሁም እርምት እንደሚወስድ መግለጹን ጠቅሱ የሀሰት ዜና ሰርቷል። ነገር ግን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባደረገው ማጣራት ጋዜጠኛው ምንም ዓይነት የመረጃ ልውውጥ ከሚኒስትር መስርያ ቤቱ ጋር እንዳለደረገ አረጋግጧል። ይህም ሆነ ተብሎ በተፈበረከ የሀሰት የፌስ ቡክ ገጽ «ከጤና ሚንስትር መግለጫ ተስጥቷል» ብሎ ዘገባ መስራቱ የጋዜጠኛውን ሀላፊነት የጎደለውና ለሙያው ስነ ምግባር ያልተገዛ መሆኑን ያመላክታል”።
3. “ከአሰራር ስርዓት እና ከተቋም አካሄድ ውጪ በተቋም ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት እንዲሁም በተቋሙ «ሰላምና መረጋጋት» እንዳይሰፍን የተለያዩ የአገልግሎት ክፍያዎች ለሆስፒታሉ ሰራተኞች እንዳልተከፈለ፥ ምንም ዓይነት መድሀኒት በተቋሙ እንደሌለ ብሎም የተለያዩ የህክምና አገልግሎቶች እንደቆሙ «ምንጫቸው የማይታወቁ» መረጃዎችን በማሰራጨት ተቋም ለማፍረስ ብዙ ሲታትር ቆይቷል። ይህ ግለሰብ ፍላጎቱ የተቋም ሰራተኞችን በሀሰት ፕሮፖጋናዳ በማነሳሳት ተቋም ለማፍረስ አለፍ ሲልም ደም ለማፋሰስ ከግብረ አበሮቹ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነ ይህ በቂ ማሳያ ነው”።
4. “ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በተሳሳተ መረጃ የተቋሙን ህልውና ለማፍረስ ቢታትርም፤ አሁንም ተስፋ አልቆረጠምና በቀን 29/08/2014 የተቋሙ የስራ ኃላፊዎችን ባላማከለ መልኩ፥ ሚዛናዊነት የጎደለውን፥ ምንጬ ያልተረጋገጠ መረጃ በማሰራጨት የተቋሙን በጎ ገጽታ ለማጠልሸት ተንቀሳቅሷል። የግለሰቡ ዓላማ አንድ እና አንድ ነው! ይህም ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ትርምስ በመፍጠር ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር በማድረግ ተቋም ማፍረስ። የሕዝብ ተቋም በሀሰት ወሬ መፍረስ እንደማይችል አላወቀም እንጂ”።
“ከላይ የተገለጹት ማሳያዎች ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት የጋዜጠኝነት የሙያ ስነ ምግባርና መርህዎን ሆነ ብሎ በመዘንጋት፤ ብዙዎችንም በሀሰት መረጃ በማነሳሳት በብዙ መልኩ እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ማሳያ ሲሆን፤ ግለሰቡ ለእውነት በመቆም ሚዛናዊ ሆኖ ታሃማኒነት ያለውን ዘገባ በመስራት ሐላፊነቱን መወጣት ሲገባው ለአንድ ወገን ያጋደለ በሚመስል መልኩ የሀሰት መረጃን ሰርቶ በማሰራጨት የዘገባ መርህን ሆነ ብሎ እየሳተ ይገኛል። ይህ ድርጊቱ በምንም መልኩ ከተጠያቂነት ነጻ ሊያወጣው አይችልም”።
“ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በፈጣን የለው ጉዞ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲው የሚተዳደረው ኮምፕሬሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም በብቁ እና በስነ ምግባር በታነጹ የህክምና ስፔሻሊስቶች አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ነው። በቅርቡም ከጤና ጥበቃ ሚንኒስቴር የተላኩ ገምጋሚ/ የሱፕርቪዥን ቡድን አባላት ሆስፒታሉ በሚሰጠው አገልግሎት ተገቢውን መስፈርት በማሟላትና ብቁ መሆኑን በማረጋገጥ የብቃት ማረጋገጫ እውቅና ማግኘቱ ይታወሳል”።
ይሁን እንጂ፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን መነሻ በማድረግ የሀሰት መረጃን በማሰራጨት ተቋሙና አካባቢውን የሁከትና የብጥብጥ ቀጠና ለማድረግ ብሎም በሰዎች መካከል ጠብ በመዝራት ደም ለማፋፋሰስ ከሽብር ሽርከኞቹ በርካታ ሚልዮን ብር ተከፍሎት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ባደረገው ማጣራት ለማረጋገጥ ችሏል።
“በአጠቃላይ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲን በተመለከተ በጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት የሚሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ በማንኛውም መስፈር ተቀባይነት እንደሌለው የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ያሳወቀ ሲሆን፤ በተሳሳተ መረጃ የተቋሙን ስም እያጠለሸ የሚገኘው ይህ ጋዜጠኛ በሕግ አግባብ ተጠይቆ ማብራሪያ ሊሰጥ እንደሚገባ ጭምር የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አቋም ይዟል”።
“በመሆኑም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት፣ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ፣የኢ.ፌ.ድ.ሪ ጤና ሚኒስቴር፣ የደቡብ ክልል አስተዳደር፣ የዎላይታ ዞን አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታችሁ አካላት ሁሉ ይህ በእኩይ ድርጊት ተቋምና ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ጋዜጠኛ በሕግ አግባብ እንዲጠየቅና ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንድታደርጉልን እንጠይቃለን” ስል የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ማምሻውን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የላከው ዝርዝር መግለጫ ያመለክታል።