

በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ «የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልፅግና» እና «አገራዊ ለውጡና የልሂቃኑ ተሳትፎ»በሚል መሪ ቃል ከዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዘርፍ አመራሮች እና መምህራን ጋር ውይይት ተካሄደ።
መድረኩ በወቅታዊ ሀገራዊና አከባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ የንቅናቄ መድረክ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፤ ሰላምንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ሁሉም ሰው ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት ተጠቁሟል።

የውይይት መድረኩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ፥ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሮ (ዶ/ር) እንዲሁም የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባልና የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አክሊሉ ለማ መርተውታል።
በውይይት መድረኩ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ፤ ዩኒቨርሲቲው ለሰላም፣ ለትምህርት ጥራት፣ ለምርምር፣ ለማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሆነ ገልፀዋል።
በመድረክ ከሰላምና ከሀገራዊ ጉዳይ አንፃር ምሁራን መጫወት ስላለባቸው ጉዳዮች በትኩረት እንዲወያዩም ጭምር ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሮ በበኩላቸዉ፤ በከፍተኛ ተቋማት ያሉ ዜጎችም ሆነ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና የየራሳቸውን ሚና መጫወት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም፤ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና ሰላም ማስፈን፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ልሂቃንን ማሳተፍ፣ ሥራ አጥነት መቅረፍ እንዲሁም የህዝብ ጥያቄ በአግባቡ በመመለስ መልካም አስተዳደርን በማስፈን ተኪ የለለውን ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲውና በየደረጃው በመንግስት መዋቅር ያሉ ሁሉም አመራሮች ሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች ሰላም እንዲሰፍን አይነተኛ ሚና መጫወት ይገባቸዋል ብለዋል ዶ/ር ዲላሞ።

ዜጎች ማህበራዊ ሚዲያን ለመልካም ነገር መጠቀም እንደሚገባ፤ ተቋሙ በሀገር አቀፍም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ሰላምን በማያናጋበት ሁኔታ በሀቅ ላይ የተመሠረተ ጭብጥ ለማስተላለፍ እንዲጠቀሙ አሳስባዋል።
የቢሮው ኃላፊው አክለውም፤ ካልተገራ የሚዲያ አጠቃቀምና የኮሚዩኒኬሽን ሥራ ሰው ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ አባልና የዎላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው ለአንድ ሀገር ብልጽግና የልሂቃን ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሀገር ደረጃም ሆነ በዩኒቨርሲቲዎች በሚድያ የሚወጡ ጽሑፎች ሰላምን የሚያናጉ ሳይሆን፤ ሰላምንና ልማትን፣ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ነገሮች መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አቶ አክሊሉ አክለውም፤ በከፍተኛ ተቋማት የሚነሱ ሀሳቦች ለሀገር ግንባታ የሚሆኑ፣ የሥራ አጥነት ችግር የሚቀርፉ፣ ለአካባቢው ሰው ችግር ፈቺ የሚሆኑ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው ዘጎች ለሀገር ብልጽግና እንቅፋት ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ራሳቸውን እንዲያርቁ ጠይቀዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የዜጎች ቀጥተኛ ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና፣ አገራዊ ለውጥና የልሂቃኑን ተሳትፎ፣ የለውጡ ትሩፋቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዱሁም በቀጣይ ምን መሠራት እንዳለበት የሚያትት ሰነድ ቀረቦ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ተወያይተውበታል።

ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዘገባ እንደሚያመለክተው በምሁራን ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፤ እንደድክመት የተነሱ ጉዳዮችን ወደ ዕቅድ ቀይሮ በመሥራት የሀገሪቱ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ሰላምንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን በጋራ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ ከመድረኩ ተቀምጧል።