ኮንፍራንሱ የልምድ፣ የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር የተደረገበት መሆኑን ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

በኮንፍራንሱ ማጠቃለያ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝንዳት ፕ/ር ታከለ ታደሰ በዩኒቨርሲቲዎች የሚከናወኑ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎቶች የአከባቢው ማህበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና የኢኮኖሚ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ፕ/ር ታከለ አክለውም፤ የሀገሪቱና የዩኒቨርሲቲዎች ሠላም፥ ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ ሳይንሳዊ ድፕሎማሲ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

በአካባቢ እና በሀገር ደረጃ የሚስተዋሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ ጥናት በመለየት መፍትሄ ለማበጀት በመተባበርና በአብሮነት በመስራት ተገቢ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በመምህራን ልማትና መልካም አስተዳደርን ማስፈን ወሳኝ ነው ያሉት ፕረዝዳንቱ፤ ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት የጥናትና ምርምር ስራዎች ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያመጠ በሚችሉ አቅም እንዲጎለበቱ መስራት ተገቢ እንደሆነም አሳስበዋል።

ይህን መሰሉ የምርምርና አካዳሚክ ኮንፍራንስ የፈዴራል፥ የክልል እንዲሁም የዞንና የወረዳ አመራር አካላት በማሳተፍ የምርምር ውጤቶችን መሬት ላይ በማውረድ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበት አግባብ ሊመቻች ይገባል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ወደፉት በሚዘጋጁ የአካዳሚክ ሆነ የምርምር ኮንፍራንስ ተሳታፊዎች ከተለያዩ ሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ተቀማት እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የተወጣጡ እንዲሆኑ አበክረን እንሰራለን ብለዋል ፕ/ር ታከለ።

የዩኒቨርሲቲው ሥራ የሚገልጹ በማህበራዊ ትስስር ገጾችንም ሆነ ዌብ ሳይት የምለቀቁ መረጃዎች የተቋሙን በጎ ገጽታ በሚገነባ መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ተደራሽ ይሆናሉም ብለዋል።

በኮንፍራንስ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎችም ውጤታቸውም ለተጠቃሚ ማህበረሰብ ግልጽ በሆነ ሁኔታ እንድቀመጡ ተገቢው ድጋፋዊ ክትትል ይደረጋል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።

በኮንፍራንሱ ማጠቃለያ ላይ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳን ዶ/ር መስፍን ቢቢሶ በዚህ የምርምር ኮንፍራንስ ሳይንሳዊ ይዘት ያላቸው 39 ጥናታዊ ጹሁፎች እንደቀረቡ ገልጸዋል፡፡

የቀረቡ ጥናታዊ ጹሁፎች ወደ ተግባር ሲገባ የማህበረሰብ ችግሮችን ሊፈታ በሚችል መልኩ የተዘጋጁ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፤ ጥናታዊ ጽሁፎቹ በፌዴራል፣በክልልና  በዞን ደረጃ የተያዘውን የልማት ሥራዎችን በአንክሮ የሚረደግፉ ናቸው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ዴአ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለጥራቱ ግብኣት የሚሆኑ ነገሮች በጥናትና በምርምር ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ለሆኑ ሳይንሳዊ የምርምር ሥራዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ምክትል ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል።

ኮንፍራንሱ የልምድ፣ የእውቀት እና የክህሎት ሽግግር የተደረገበት መሆኑን የጥናታዊ ጹሑፍ አቅራቢዎች ሆነ ሌሎች ተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን፤ እውቀትን ወደ ተግባር ለመቀየርና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የበለጠ ተነሳሽ ያደርጋል ብለዋል።

በኮንፍራንሱ ማጠቃለያ ለጽሁፍ አቅራቢዎች፣ ለዝግጅት አስተባባሪዎች የምስጋናና የእውቅና ማበረታቻ ምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: