

ጉግል በአፍሪካ ለኩባንያው የመጀመሪያ የሆነውን የምርት ማበልፀጊያ ማዕከል በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ፡፡
የማዕከሉ መከፈት በአህጉሪቱ እየጨመረ የመጣውን የኢንተርኔት ተጠቃሚ ማሕበረሰብ ለማገልገል የኩባንያው የቅድመ ዝግጅት እንቅስቃሴ አንዱ አካል መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2020ዎቹ መጨረሻ የአህጉሪቱ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ቁጥር ስምንት መቶ ሚሊዮን እንደሚደርስ ጉግል አስታውቋል፡፡ ከዓለም አንድ ሦስተኛ የሚሆነውን ወጣት ከመያዟ ጋር ተዳምሮ አህጉሪቷን ማራኪ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት ይጠበቃል ሲል ዘገባው አትቷል፡፡
ኩባንያው ማዕከሉን ሥራ ለማስጀመር ሠራተኞች መቅጠር መጀመሩን ዘገባው አመላክቷል፡፡
ጉግል ከዚህ ቀደም በጋና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል መክፈቱ የሚታወስ ሲሆን በዓምስት ዓመታት ውስጥ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በአህጉሪቱ ለሚሰራቸው ስራዎች ወጪ ለማድረግ ማቀዱ ተመላክቷል፡፡