
ሰበር ዜና
በዎላይታ ሮከትን ጨምሮ ሌሎች የፈጠራ ስራዎች ባለቤት የሆነው የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሙኤል ዘካርያስ ከኢትዮጵያ መረጃ ደህነነት ጋር በቅርበት ለመስራት ተመቻቸለት
“ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶን የመደገፍና የማብቃት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ” ኢመደአ
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊ ወጣት ኢትዮጵያውያንን የመደገፍና የማብቃት ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛዉ ገለጹ።

የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነዉ እና የETR S1KM ተብሎ የሚጠራ ሮኬት መስራት የቻለዉን ታዳጊ ሳሙኤል ዘካሪያስን በመቀበል በኢትዮ-ሳይበር ታለንት ማዕከል የፈጠራ ሥራዎቹን ወደተሻለ ደረጃ እንዲያደርስና በማእከሉ እንዲታቀፍ አድርገዋል።
ለተማሪ ሳሙኤል ዘካሪያስ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርግና በዚህም የአቅም ግንባታ፣ የቁሳቁስና የስልጠና ድጋፍ እንደሚደረግለት ዶ/ር ሹመቴ ግዛዉ ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ከተማሪ ሳሙኤል ዘካሪያስ ተሰጥኦዉን ለማሳደግ በሚረዱት ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።
በዉይይቱ ላይ የተማሪ ሳሙኤል የፈጠራ ውጤት ለሃገር የሚያበረክተዉ አስተዋጽዎ ከፍተኛ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሹመቴ ግዛዉ ገልጸው፤ አስተዳደሩ እንደ ሳሙኤል አይነት ታዳጊ የፈጠራ ባለቤቶችን አቅሞ በማጎልበት ለሃገር በሚጠቅም መልኩ መስራት ይገባል ብለዋል።


በተለያዩ የሃገራችን ክፍል የሚገኙና በሳይበር ደህንነት እና ተያያዥ ዘርፎች ባለ ልዩ ተሰጥዎ ታዳጊዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በመዉሰድ ህልማቸዉን ለማሳካት አስተዳደሩ የራሱን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም ዶ/ር ሹመቴ ግዛው መግለጻቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።