
በዎላይታ ዞን በዳሞት ሶሬ ወረዳ የሱንቃሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አቶ ከበደ ካንሱራ በግል ማሳቸው የወንዝ ውሃን በመጥለፍ ዓሳ ማምረት ችለዋል፡፡
አቶ ከበደ ካንሱራ በሱንቃሌ ቀበሌ አንጩቾ 01 ቀጠና በ2011 ዓ.ም በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ ድጋፊ የዓሳ ማርባት ሥራ የጀመረ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት የዓሳ ምርትን በመሸጥ የተሻለ ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም በዘንድሮ ዓመት ዓሳን ምርትን የሚገዙ ግለሰቦች እየመጡ አለመሆናቸውን ገልጸው የዓሳ ምርትን የሚፈልጉ አካላት መጥተው መግዛት እንደሚችሉም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ከበደ ገለፃ ይህንን ሥራ እንድጀምር ያነሳሰው በጓሮ በኩል ዓመት ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሰዉ የመሬ ወንዝ ለዚህ ሥራ ልጠቅመኝ እንደሚችል በማሰብ ያለኝን ፍላጎቴን ወደ ተግባር ለመቀየር አስችሎኛል ብለዋል፡፡
በዚህም የወረዳዉ መንግስት እና የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ አስፈላጊውን ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ማድረጉን እና የወረዳዉ እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ሙያዊ ምክርና ድጋፊ እያደረገ ነው ብለዋል።
ሙያዊ ድጋፊ ለዓሳ እርባታ ተጠናክሮ ከቀጠለና የገበያ ዕድሎች ከተፈጠረለት አስፍተዉ ለመሥራትና የዶሮ እርባታንም ለመሥራት ዕቅድ ማዘጋጀቱን ተናግረዉ ማንም ሠዉ ጠንክሮ መስራት ከቻለ መለወጥ እንደምችልም ገልጾልናል።
አቶ ከበደ ከዓሳ ማርባት ባሻገር የግብርና ሥራን በዘመናዊ መንገድ በማዘመን የተለያዩ የጓሮ አታክልቶችን እያመረት እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
አርሶአደሩ የተፈጥሮ ዝናብን ሳይጠብቅ የአፈርና ዉሃ ጥበቃ ሥራ ሰርተዉ በጄነሬተር ዉሃ ፓምፕ ተጠቅመዉ ቀይ ሽንኩርት፣ የሀበሻ ጎመን፣ ጥቅል ጎመን፣ በቆሎና ሌሎች ሰብሎችን ቦሎቄን ጨምሮ በመዝራትና የከብቶችን መኖ በማዘጋጀት ለአከባቢዉ ማህበረሰብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሞዴል አርሶ አደር ሊሆን ችሏል።

በተቀናጀ የዶሮ፣ ዓሳ እና የጓሮ አትክልት ልማት ለተሻለ ገቢ እና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የገቢ አቅምን ከመጨመሩ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል፡፡
ዓሳን በማምረት ለምግብ ፍጆታነት መጠቀም መጀመሩን የተናገሩት አርሶ አደሩ የዓሳ ምርትና ምርታማነትን የበለጠ በማሳደግ የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲጠቀም ለገብያ እያቀረበ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡