
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2014 24ኛ ሳምንት የዲሲፕሊን ውሳኔዎች።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሐሙስ ግንቦት 11 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በ24ኛ ሳምንት የተደረጉ ግጥሚያ(ዎችን) ጨምሮ ሌሎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ ውጤት በማፅደቅ እንዲሁም የዲሲፕሊን ሪፖርትም ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።
በተጫዋቾች አላዛር ማርቆስ (ጅማ አባ ጅፋር) ፣ ተስፋዬ መላኩ(ጅማ አባ ጅፋር) ፣ አቡበከር ናስር(ኢትዮጵያ ቡና)፣ ጸጋዬ አበራ(አርባምንጭ ከተማ)፣ ፉዓድ ፈረጃ(ባህርዳር ከተማ) እና ዮሴፍ ዮሀንስ(አዳማ ከተማ) በተለያዩ የክለባቸው ጨዋታዎች አምስተኛ ቢጫ ካርድ በማየታቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም ዊሊያም ሰለሞን(ኢትዮጵያ ቡና) አስረኛ ቢጫ ካርድ በመመልከቱ ለፈፀመው ጥፋት ሁለት ጨዋታ እንዲታገድ የገንዘብ ቅጣት ብር 2000 /ሁለት ሺህ/ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፏል።
በክለቦች አርባምንጭ ከተማ ፣ አዲስ አበባ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና የክለባቸው የተለያዩ አምስት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ቢጫ ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ እንዲሁም ወላይታ ድቻ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን የጨዋታ አመራሮች በተደጋጋሚ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበትና ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው ክለቡ መቀጣቱን በዚህም ደጋፊዎቹ ከድርጊታቸው አለመማራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር የ75000 /ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲቀጣ ተወስኗል ።
ሶስት ዳኞች ወደ መጡበት እንዲመለሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውሳኔ አስተላለፈ
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች 12 በጨዋታ 3 በፍጹም ቅጣት ምት በድምሩ 15 ጎሎች ሲቆጠሩ 49 ቢጫ ካርድ እና አንድ ቀይ ካርድ በተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች ላይ ተመዟል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ውጤት ማጽደቅና የጨዋታ ታዛቢዎች ሪፖርት ለማየት በትናንትናው እለት ባደረገው ስብሰባ ከዳኝነት አንፃር ክስ የቀረበባቸውን ጉዳዮች ለብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ለውሳኔ አስተላልፏል።



በሳምንቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች ወላይታ ድቻን ከ ሲዳማ ቡና ያጫወቱት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ እና ረዳት ዳኛ አብዱ ይጥና ውጤት የሚያስቀይር ስህተት መስራታቸው እንዲሁም ሀድያ ሆሳዕናን ከኢትዮጵያ ቡና ያጫወተው ዋና ዳኛ ሚኬሌ ጠዓመ ተጫዋችን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደቡ ሪፖርት ከመደረጉ በተጨማሪም ለየጨዋታዎቹ በዎላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የቴክኒክ ክስ ቀርቦባቸዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴም ሶስቱን ዳኞች ለጊዜው ውድድሩ ከሚካሄድበት ባህር ዳር ከተማ ወደ መጡበት ከተማ እንዲመለሱ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ቀጣይ ውሳኔዎችንም በሂደት እንደሚገልፅ ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ አሳውቋል።