a_1653058652315

የዎላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ሊቀመንበርነት ውዝግብ ዙሪያ በዎላይታ ታይምስ ሚዲያ መረጃ ተሰብስቧል።

የፓርቲው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ የፓርቲው አመራሮች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት የፓርቲው ሊቀመንበር ጉባኤውን ለመጥራት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው እንዲሁም የተፈጠረው አለመግባባት የግንባሩን ሕልውና የሚያናጋ እና አስጊ ወደሆነ አቅጣጫ የሚያመራ በመሆኑ ችግሩን በጉባኤ ለመፍታት ጉባኤ መጥራት የወሰነ እና የቦርዱ ታዛቢ እንዲላክለት ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ማሳወቁን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከቦርዱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በፓርቲው ደንብ መሠረት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት የሚችለው ለፓርቲው ሊቀመንበር በቅድሚያ አስቸኳይ ጉባኤውን እንዲጠራ ካሳሰበ እና ሊቀመንበሩም ይህን ተከትሎ አስቸኳይ ጉባኤውን ለመጥራት ፍቃደኛ ያልሆነ ከሆነ መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም ቦርዱ የፓርቲው ሊቀመንበር በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት እስከ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲጠሩ፥ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ስላደረጉት ዝግጅት እንዲሁም ጉባኤውን ለመጥራት ያለውን ዝርዝር እቅድ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ይህ ካልተፈፀመ በፓርቲው መተዳደሪያ መሠረት የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አስመራጭ ኮሚቴና ጊዜያዊ ሊቀመንበር በመሠየም ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ሥልጣን ያለው መሆኑን ቦርዱ ለፓርቲው ሊቀመንበር እና ለኢንስፔክሽን ኮሚሽኑ ቦርዱ ገልጿል፡፡

ከዚያ መነሻ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በአሁኑ ወቅት ህጋዊ የፖርቲው የዎላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ዎሕዴግ) ሊቀመንበር ማነው በሚል ውዝግብ ዙሪያ ከሁለቱ ሊቀመንበርነት ይገባኛል ያነሱ አቶ ተክሌ ቦራና እና ከአቶ ጎበዜ ጎኣ አነጋግሮ ተከታዩን መረጃ አግኝቷል።

አቶ ተክለ ቦረና በጉዳዩ ተጠይቆ “የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በጥር 1/2013 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ እኔ በ87 ድምፅ ከሁሉም አብላጫ አግንቼ የተመረጥኩ ቢሆንም በማላቀው ሁኔታ የፖርቲው ምክትል ነህ ተባልኩኝ፣ ውሳኔውን አልቀበልም ብዬ ለምርጫ ቦርድ አቤቱታ አስገብቻለሁ” ብለዋል።

“በዕለቱ የምርጫ አስፈፃሚ ተብሎ የተሰየሙ ግለሰቦችም ገለልተኛ ያልነበሩና የተቆጠረውን ድምፅ በተገቢው ያላከበሩ ማለት ይቻላል፣ ለዚያም ነው እንኳን ለፓርቲው አመራርነት እጩ ማድረግ፦ የፓርቲው አባል ያልሆነውን ግለሰብ በተጭበረበረ መንገድ ሊቀመንበር ብሎ ስለሰየሙት አቤቱታ ለምርጫ ቦርድ ለማስገባት የተገደድኩት” በማለት አቶ ተክለ በተለይም “ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተናግረዋል።

“አሁን ላይ ህጋዊ የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር እኔ ነኝ፣ የምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጋችሁ የውስጥ ክፍተት እንድስተካከል በሚል ባዘዘን መሠረት ሰኔ 4/2014 ዓ.ም ጉባኤውን ለማካሄድ ዝግጅት እያደረግን ነው” በሚል አቶ ተክሌ ቦራና አክለው በነበረን ቆይታ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አቶ ጎበዜ ጎኣ በጉዳዩ ዙሪያ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ምላሽ ሲሱጡ “የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በጥር 1/2013 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ከሁሉም አብላጫ አግንቼ በዋና ሊቀመንበርነት እየመራ ያለው እኔ ነኝ፥ ምርጫ ቦርድ አንድ ግለሰብ ባስገባው አቤቱታ መነሻ በምርጫ ወቅት ለሁለም ፓርቲዎች የሚሰጠውን ድጋፍ አግዶ በስራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሯል” በሚል ምርጫ ቦርድ ላይ ቅሬታ አቅርቧል።

ግንባሩ “በጥር 1/2013 ዓ.ም ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ የቀድሞ የፓርቲውን ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረናን ከፓርቲው ሊቀመንበርነት አንስቶ እኔን የፓርቲው ሊቀመንበር በማድረግ አዲስ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አደራጅቶ በወጣትና በነባር አመራሮች የዎላይታ ህዝብ መፃኢ እድል ላይ በአሉታዊነት የሚቃጣን ኃይል ለመታገል ለዎላይታ ህዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን ለዎላይታ ህዝብ ነፃነትና እኩልነት እንዲሁም የራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ መብቱ እንዲረጋገጥ እየታገለና እያታገለ የሚገኝ የዎላይታ ህዝብ ፓርቲ ነው” ብለዋል አቶ ጎበዜ።

“የቀድሞ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ተክሌ ቦረና ከድርጊቱ እንድታቀብ በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም እምቢ አሻፈረኝ በማለቱ” የፓርቲው ማዕከላዊ ምክርቤት ከየትኛውም ፓርቲን በሚወክሉ ጉዳዮች ላይ እንዳይሳተፍ፣ በፓርቲው ስም ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳይሰጥ፣ የፓርቲውን ስም ተጠቅሞ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ በማገድ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውን አቶ ጎበዜ አብራርተዋል።

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚህን ሰዓት የፓርቲ ህጋዊ ሊቀመንበር ማነው በሚል ለጠየቀው ጥያቄ አቶ ጎበዜ “አሁን ላይ ህጋዊ የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር እኔ ነኝ፣ የምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ አድርጋችሁ የውስጥ ችግር በጉባኤው እንድስተካከሉ በሚል ባዘዘን መሠረት እስከ ሰኔ 10/2014 ዓ.ም ድረስ በኮሚቴ ወስኔን ጉባኤውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው” በሚል በነበረን ቆይታ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቦርዱ የፓርቲው ሊቀመንበር በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት እስከ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን እንዲጠሩ፥ የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ስላደረጉት ዝግጅት እንዲሁም ጉባኤውን ለመጥራት ያለውን ዝርዝር እቅድ እስከ ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም ለቦርዱ እንዲያሳውቁ በተጠየቁት መሠረት አቶ ጎበዘ ጎኣ ለምርጫ ቦርዱ ማስገባታቸውን የገለፁ ሲሆን አቶ ተከሌ ቦረና ደግሞ በተለያዩ ምክንያት ለማስገባት የዘገየ መሆኑን በመግለፅ በነገው ዕለት ለምርጫ ቦርድ ለማስገባት ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

አቶ ተክለ ቦራና “ሰኔ 2/2014 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው” ያላሉ፤ አቶ ጎበዜ ጎኣ ደግሞእስከ ሰኔ 10/2014 ዓ.ም ድረስ በኮሚቴ ወስኔን ጉባኤውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረግን ነው” በሚል ምላሽ ሰጥተዋልና በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት ያለው ጠቅላላ ጉባኤ የማን ይሁን ? በጉዳዩ ዙሪያ ምርጫ ቦርድ የውስጥ ችግራቸው በጠቅላላ ጉባኤው ይፈታል ከማለቱ ውጪ ሌላ ምላሽ አልሰጠም።

በጉዳዩ ዙሪያ ሀሳብ በመስጠት የተባበሩ አቶ ተክሌ ቦራና፣ አቶ አቶ ጎበዜ ጎኣን እንዲሁም ምርጫ ቦርድን እያመሰገንን ቀጣይ ጉዳዩ የደረሰበትን ደረጃ እንደምናቀርብ ከወዲሁ እንገልፃለን።