has3

በዎላይታ ዞን በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ጉልጉላ ቀበሌ ከተማ ማዘጋጃ ውስጥ “ካናቢስ” የተባለውን አደንዛዥ ዕጽ ሲያመርቱ ተደረሰባቸው

የሶዶ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል በህብረተሰብ ጥቆማ መሠረት «ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እጽ በማሳቸው ሲያመርቱ ደርስኩባቸው» ያላቸውን ሁለት ሰዎች ይዞ አስሯል።

በሶዶ ዙሪያ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወረዳ ማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል አስተባባሪና ረ/ኢ/ር ደርጉ አሣሌ ዛሬ እንዳስታወቁት ተጠርጣሪዎቹ ሊያዙ የቻሉት በግል ማሳዎቻቸው “ካናቢስ” የተባለ አደንዛዥ እጽ ተክለው እንደሚገኙ ፖሊስ ከህብረተሰብ ከደረሰው ጥቆማ መሠረት እንደተቆጣጠራቸው ረ/ኢ/ር ደርጉ ተናግረዋል።

ከአርሶ አደሩ ማሳ የተገኘዉ የእጽ ናሙና ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ዞን ፖሊስ መምሪያ ተልኮ ተክሉ “ካናቢስ” በመባል የሚታወቀው አደንዛዥ እጽ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉንና ከማሳዎቹ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ መደረጉንም አስረድተዋል።

ረ/ኢ/ር ደርጉ አክለውም «ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወረዳው ከአህል ምርት ጋር በማቀላቀል የአደንዛዥ እጽ ተክሎችን በአርሻ ማሳዎች ውስጥ የማምረት አንቀስቃሴ እየተስፋፋ ይገኛል። በአኛ በኩል ኅብረተሰቡ የካናቢስ አይነቶችን በቀላሉ ለመለየት እንዲችል የፎቶግራፍ ቅጂዎችን በማባዛት ለሁሉም የቀበሌ መስተዳድሮች እሰራጭተናል።

ይህም በቀጣይ በተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦች ሲያጋጥሙ እጹን በቀላሉ በመለየት ለሕግ አካል ጥቆማ ለመስጠት ያስችለዋል» ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት አቅርቦ ለማስቀጣት የናሙና ምርመራ ውጤት፣ የኤግዚቢትና ሌሎች ተያያዥ ማስረጃዎችን የማደራጀት ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ረ/ኢ/ር ደርጉ ጨምረው ገልጸዋል።