

የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናት ጤና ልማት ላይ ያተኮረው የአድቮከሲ ኮንፍራንስንየቀድሞ የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ አስጀመሩ
የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከደቡብ ኦሞ ዞን ጋር በመተባበር “የተቀናጀ የጋራ ጥረት ለፈጣንና ተመጣጣኝ የእናቶች፣ የጨቅላ ህጻናትና ህጻናት ጤና ልማት” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የከፍተኛ ልዑክ የአድቮከሲ ኮንፍራንስ በዛሬው እለት በሐመር ወረዳ ዲመካ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የኮንፍራንሱ ዓላማ ፋውንዴሽኑ በአርብቶ አደር ወረዳዎቹ በሚሰራቸው የእናቶች፣የጨቅላ ህፃናትና የህፃናት የጤና ልማት ሥራዎች የአከባቢው ነዋሪዎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እንዲሆኑ ለማስቻል ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።

የከፍተኛ ልዑክ ቡድኑ በሐመር ወረዳ አስተዳደር፣ የጎሳ መሪዎች፣ባላባቶችና ከማህበረሰቡ በተወጣጡ አካላት ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን ማህበረሰቡ ለቀድሞ የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት እና የኃይለማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ክብርት ወ/ሮ ሮማን ተስፋዬ ስጦታ በማበርከት ፋውንዴሽኑ በወረዳው ለሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ያላቸውን አድናቆት መግለፃቸውን ከፋዉንዴሽኑ የተላከልን ዘገባ ያመለክታል።