1655907367912

ሰሞኑን በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ግድያዎችን አስመልክቶ ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ በተለይ በኦሮምያም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችና ግጭቶች ለንጹሃን ዜጎች ሞት፤ ስቃይና መፈናቀል ምክንያት መሆኑን በመግለፅ ከሰሞኑ ሰኔ 11 2014 ዓም ወዲህ በኦሮምያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ አካባቢ በተፈጸመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ዜጎች እንደተገደሉ ሰምተናል” ከሞቱትም አብዛኞቹ ሴቶችና ህፃናት እንደሆኑ መረጃዎች እንደሚያሳይ ፓርቲው በመግለጫው ገልጿል፡፡

በዚህ የጅምላ ግድያ መንግስት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን ሲከስስ፤ ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ የመንግስት ታጣቂዎችን ይኮንናል፣ በተለያዩ ጊዜያት የሕዝብን ሕሊና ያስጨነቁ መንግስታዊም ሆነ ከመንግስት ውጪ ያሉ የታጠቁ ኃይሎች የሚፈጸሙት አሰቃቂ ግድያዎች በቪዲዮ ጭምር እየተቀረጹ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተለቀዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህን አጸያፊ ተግባሮች ለመቆጣጠር፤ አጥፊዎችን ለመያዝም ሆነ ወደ ሕግ ለማቅረብ የሚደረግ የጎላ እንቅስቃሴ አይታይም ብሏል፡፡

ለማሳያም በያዝነው 2014 ዓም በታህሳስ ወር የመጀመሪያ ሳምንት በመንግሰት እዝ ስር በነበረውና የመንግሰት የፀጥታ ኃይሎች ያሉበት የዘመቻ ሚኒሊክ አባላት በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ዳዋ ጫፋ ወረዳ ልዩ ስሙ እንቶሊ በሚባል ስፍራ የኦነግ ሸኔ አባላት ናቸው ያሏቸው ሰዎችን ከመኪና እያወረዱ የፈጸሙት አሰቃቂ ግድያ በቪዲዮ የተቀረፀና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተጣርቶ የቀረበ ቢሆንም እስካሁን የተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ አይታወቅም ስል ፓርቲው አብራርቷል።

እንደ ኦፌኮ አመራር ግንዛቤ የንጹሃንን ደም በማፍሰስ ሊገኝ የሚችል ምንም አይነት የፖለቲካ ትርፍም ሆነ ድል ሊኖር እንደይችል ከልብ እናምናለን፡፡ በንፁሃን ላይ የሚፈጸሙ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃቶችን እናወግዛለን፡፡ በኦሮምያ የሚኖሩ የሌላ ብሄር ተወላጆች እንደማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ጥበቃና ለሕይወትና ንብረታቸው ሙሉ ዋስትና ማግኘት ይገባቸዋል የሚል ፅኑ እምነት አለን፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮምያ ብሄራዊ ክልል እና የፌዴራሉ መንግስtaት ኃላፊነታቸውን ሳያሰልሱ ሊወጡ ይገባልም ብሏል በመግለጫው፡፡

ኦፌኮ በሃገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የተፈጸሙ ግድያዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩና አጥፊዎችም ለፍትህ አካል እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ እንደቆየ ሁሉ፤ በቶሌው የንጹሃን ጭፍጨፋም ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በሙሉ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ አጥፊዎችም ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በጥቃቱ ሕይወታቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸን፤ ለወዳጅ ዘመዶቻው መፅናናትን እንመኛለን፡፡ ከጥቃቱ የተረፉትን ለማረጋጋትና በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ እናስገነዝባለን ብሏል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጸሙ ጥቃቶችና የንጹኃን ግድያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ዋና ምክንያት እንረዳለን፡፡ ስለዚህ በፖለቲካ ልዩነት ወደ ጦርነት የገቡ ኃይሎች ልዩነታቸውን በማጥበብ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ድርድር በማድረግ ጦርነት እንዲያቆሙ እናሳስባለን ሰል የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመግለጫው ጠይቋል።