ዩኒቨርሲቲው በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የዎላይትኛ ቋንቋ ሰዋሰው መጽሐፍ ለማሳተም ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ተገለፀ

ልምድ ያላቸው የቋንቋ መምህራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚታተመው መጽሐፍ ላይ ግምገማዊ ውይይት አካሂደዋል።

ዩኒቨርሲቲው በባህልና ቋንቋ ልማት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።

በዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ በዎላይታቶ ቋንቋ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ትኩረቱን የዎላይትኛ ቋንቋ ሰዋሰው መጽሐፍ ሕትመት ዝግጅት ላይ ያደረገ አውደ ምክክር ተደርጓል።

በአውደ ምክክሩ ከዩኒቨርሲቲው ዎላይታቶ ቋንቋ ትምህርት ክፍል መምህራን እንዲሁም ከውጭ ከተጋበዙ የዘርፉ ሙሁራንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸው ተጠቁሟል።

በመጽሐፉ አጠቃላይ ዝግጅት እና የሰዋሰው አጠቃላይ ዕይታና አቀራረብ ላይ ትኩረት በማድረግ ገምጋሚዎች እና የተሳታፊዎች አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

የዎላይታቶ ቋንቋ ሰዋሰው ስርዓት ጽንሰ-ሀሳብ ላይ ተመስርቶ በተዘጋጀ እና በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው መጽሐፍ ለሕትመት ዝግጁ መሆኑ በመድረኩ ተገልጿል።

መጽሓፉ የተሟላ የዎላይታቶ ሰዋሰውን በማካተት በስምንት (08) ምዕራፎች የተዘጋጀ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ለመማር ማስተማር ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለማጣቀሻነት እንደሚያገለግል ነው የተገለጸው።

በመድረኩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳዊት ዳልጋ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሦስት አመታት ዘርፈ ብዙ የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራት ማከናወኑን ተናግረዋል።

የቅድምያ ቅድምያ ተሰጥቷቸው ተግባራዊ ከተደረጉ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች በቋንቋ ልማት መስክ አንዱ የዎላይታቶ ቋንቋ ሰዋሰው መጽሐፍ ማሳተም እንደሆነ ዶ/ር ዳዊት ጠቁመዋል።

መጽሐፉ ለሕትመት ብቁ ሆኖ መዘጋጀቱን በባለሙያዎች ለማስገምገምና ለማስተቸት ይህ መድረክ መዘጋጀቱን ዳይሬክተሩ አሳውቀዋል።

መጽሃፉ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ታትሞ ለማህበረሰቡ ተደራሽ እስከሚሆን ድረስ አስፈላጊው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዶ/ር ዳዊት ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *