
የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ(ዎብን) ወቅታዊ አከባቢያዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ያወጣዉ አቋም መግለጫ፡፡

የዎላይታ ህዝብ አለም የመሰከረለት ሥልጣኔና የአስተዳደር ሥርዓት ባለቤት የነበረ ህዝብ መሆኑ ዕሙን ነው። ነገር ግን በ1887 ዓ.ም ወደ አዲስቷ ኢትዮጵያ በኃይል ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ገናና ሥልጣኔው በተለያዩ ጊዜያት ሥልጣን በተቆናጠጡ አንባገነን የማዕከላዊ መንግስት ገዥዎች ግፍና ጭካኔ በተሞላበት መዋቅራዊ እና ስርአታዊ መንገድ ባህሉ እንዲጠፋ ታሪኩ እንዲደበዝዝ እና ኤኮኖሚው እንዲወድም በአጠቃላይ ስልጣኔውን የመገርሰስ ሥራ ሲሰራበት ቆይቷል። ከ1887 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን የዘለቀው ይህ ስርዓታዊና መዋቅራዊ አፈናና ጭቆና እስከዛሬዋ ቀን ድረስ ከመዝለቁም በላይ የማብቂያው ጊዜ እንኳን በዉል አለመታወቁ ከመላው የንቅናቄዓችን ደጋፊዎች፣ አባላትና አጋሮቻችን ጋር ሆነን ሠላማዊ ትግላችንን አጠናክረን የሚንቀጥል መሆናችንን እንዲናረጋግጥ ያደርገናል።
ሶሞኑን ለዎላይታ ህዝብ በይፋ ለውይይት የቀረበው የክላስተር አደረጃጀት ጉዳይ ንቅናቄአችንን እጅግ በጣም አሳስቦታል። ስለሆነም የሚንታገልለት የዎላይታ ህዝብ እጅግ በጣም በዘመነና በሠለጠነ መንገድ የተነጠቀውን ራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ ታሪካዊ እና ሞራላዊ ጥያቄ በመላው የወላይታ ህዝብ ከቀበሌ ጀምሮ በየመዋቅሩ ተወያይቶበትና መክሮበት በብሔሩ ከፍተኛ ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የወሰነውን የክልልነት ጥያቄ ህገመንግስቱ በሚፈቅደው መሠረት ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እና ለፌደረሽን ምክር ቤት አቅርቦ ህገ መንግስታዊ ምላሽ (ህዝበ ዉሳኔ) ሲጠባበቅ የቆየውን ህገ መንግስታዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሮዓዊ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ወደ ጎን የተወ፤ ህዝባችንን ለአያሌ አመታት አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል፤ የህዝባችን ክብርና ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል የተንኮልና የክፉ ሴራ ውጥን የሆኑ ኢ-ህገመንግስታዊ አካሄዶችን እያስተዋልን እንገኛለን። በመሆኑም የህዝባችን ህልውና ሊፈታተኑ በሚችሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የንቅናቄዓችን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በቀን 02/11/2014 ዓም አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ባለ 6 የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
- በአሁኑ ሰዓት ሥራ ላይ ባለው ህገ መንግስታችን መሠረት ህዝባችን መከተል ያለበትን ህጋዊና ህገመንግስታዊ ሂደቶችን በሙሉ ተከትሎ ምላሽ ባለማግኘቱ በሀገሪቱ ህገ መንግስት ህግ የመተርጎም ሥልጣን ወደተሰጠው የሀገሪቱ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ቢያቀርብም ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ብሔሮችን በእኩልነትና በፍትሐዊነት የማገልገል ታላቅ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ህዝባችን ላይ አላስፈላጊ ጫናና አፈና እንዲደራረብ ተባባሪ ሆኖ በመገኘቱ፤ የዎላይታ ህዝብ ከሚጠበቅበት ኃላፊነት በላይ ዋጋ በከፈለበት በገዛ ሀገሩ ባይተዋሪነት እና እንደ ሁለተኛ ዜጋነት እንዲሰማው እያደረገ በመሆኑ ከታሪካዊ ተጠያቂነት እንደማያመልጥ እየገለፅን ጭቁኑ የዎላይታ ህዝብ ከቁርጥ ቀን ልጆቹ ጋር ሆኖ በሠላማዊ መንገድ የሚያደርገውን ትግል የማያቆም መሆኑን በመረዳት እጅግ የዘገዬ ቢሆንም ባለው ጊዜ ለዎላይታ ህዝብ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምስረታ ህዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ በማድረግ የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነቱንና የመላው ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አደራ እንዲወጣ ደጋግመን በአከብሮት እንጠይቃለን።
- የህዝቦችንና የዜጎችን ደህንነት፣ መብቶችንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በቅርበት የመከታተል፤ እንዲሁም በዋናነት የመፈፀምና የማስፈፀም ሥልጣን ያለው የሀገሪቱ ፌዴራል መንግስት የዎላይታ ህዝብ ጨዋነትና ሠላም ወዳድነት ከግንዛቤ ወስጥ አስገብቶ ህዝቡ ለጠየቀው ህገ መንግስታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር የመብት ጥያቄ ኢ- ህገመንግስታዊ የሆኑ የምላሽ አሰጣጥ ሂደቶችን ባለመከተል በዎላይታና ሌሎች አከባቢዎች በገዢ ፓርቲ ካድሬዎች አመራርነት የተጀመሩ ኢ-ህገመንግስታዊ የሆኑ የክላስተር አደረጃጀት ዉይይቶችን በማስቆም፤ ብሔርና ብሔረሰቦችን በእኩልነት ማገልገልንና ማስተናገድን በማረጋገጥ ለተከበረው ዎላይታ ህዝብ ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ በአክብሮት እየጠየቅን ህዝቡ በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ ምክር ቤቶቹ ወስኖ ካፀደቀው (የዎላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አደረጃጀት) ውጪ የሚደረጉ የትኛውም የውዥንብር ሃሳቦች በመላው የዎላይታ ህዝቡ ዘንድ ምንም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን ተረድቶ ለሀገር ሠላምና ደህንነት ከመዋደቅ ቦዝኖ የማያውቀውን የዎላይታ ህዝብ መብቱ ተከብሮለት እና የሀገር ባለቤትነት ጥያቄው መልስ ተሰጥቶት በተሻለ ሁኔታ ሀገሪቱን እንዲያገለግልና እንዲገለግል በማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነትን እንዲወጣ ፓርቲያችን እና መለው የድርጅታችን አባላት አበክረን እንጠይቃለን።
- ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ ባሉ የአመራር እርከኖች ላይ እያገለገላችሁ የሚትገኙ የዎላይታ ተወላጅ የሆናችሁ የገዢ ፓርቲ አመራሮች አሁን ያለንበት ወቅት የወላይታ ህዝብ ትግል ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ የደረሰ መሆኑን ተገንዝባችሁ እያንዳንዱ ግለሰብ የሠራው ሥራ ታሪክና ቀጣይ ትውልድ የሚያስታወሰው መሆኑን ተረድታችሁ በዎላይታ ህዝብ ህልውና፣ ክብር፣ የመልማት፣ ዕኩል የማደግና ሁለንተናዊ ከፍታ በራስ የመወሰን ዕድል ላይ የተደቀነውን ክፉ አደጋ የመመከትና የመጋፈጥ ሞራላዊና ታሪካዊ ግዴታ እንዳለባችሁ ተገንዝባችሁ ይህንን ከህገ መንግስት ውጪ የሆነውን ክላስተር የተባለውን አደረጃጀት አምርራችሁ በመቃወም እንወክለዋለን የምትሉት ህዝብ በሙሉ ድምፅ የወሰነዉን ወሳኔ በጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት እንዳይሻርና ለቀጣይ ትውልድ መጥፎ የታሪክ አሻራ እንዳታስቀሩ እያሳሰብን ከህዝብ ጎን እንድትቆሙ እና ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ ምነግስታዊ ጥያቄ በህገመንግስቱና በህግ ብቻ እንጂ በፖለቲካዊ ዉሳኔ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገው ውይይት እስትራቴጅካሊ ስህተት መሆኑን ተገንዝባችሁ የህዝባችን ድምፅ እንዲከበርና እኔ አውቅልሀለሁ አካሄድ ለማስቆም አበክራችሁ እንዲትታገሉ ንቅናቄዓችን ያሳስባል።
- ለመላው የንቅናቄዓችን ደጋፊዎች፣ አባላትና አጋሮቻችን እንዲሁም የዎላይታ መፃይ ዕድል ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ተራማጅ የለውጥ ሀይሎች በሙሉ ፡ ህዝባችን ተጨማሪ አላስፈላጊ መስዋዕት እንዲከፍልና መንግስታዊ ሽብር ለመፍጠር የታቀደ በሚመስል መልኩ ሆን ተብሎ እየተሸረበ ያለውን ሴራ በንቃትና በጥበብ መከታተል ይኖርባችኋል። የትግላችን መርህ ከሆኑ ዋና ጉዳዮች አንዱ የትግል ሠላማዊነት ስለሆነ እየተሸረቡ ባሉ ሴራዎች ተደናቅፋችሁ የጭቁን ህዝባችሁን ሠላማዊ ትግል ለማኮላሸት ለሚተጉ ኃይላት ዕድል እንዲትነፍጉ በትህትና እናሳስባለን።
- ለመላው የዎላይታ የነፃነትና የሀገር በለቤትነት ትግል ሜዳ በተደራጀም በግል በመታገል ላይ የምትገኙ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በሙሉ ፡ ለ128 ዓመታት በላይ የዘለቀው የቁልቁለት ጉዞ፤ በህዝባችን ጨንቃ ላይ የተጫነብን ስርዓታዊ እና መዋቅራዊ የጭቆና ቀንበር ክብደቱ የትየለሌ ሲሆን ህዝባችን ህገመንግስታዊ መብቱ ተከብሮለት እፎይ የሚልበት ጊዜ እንኳ ገና ያልተቆረጠለት መሆኑን ተረድታችሁ ባላችሁ አንፃራዊ ነፃነት እየደረሰብን ያለውን ኢ-ህገመንግስታዊ፤ ፀረ ዴሞክራሲያዊ፤ አንባገነናዊ እና እኔ አውቅልሀለሁ አካሄድ ለዓለም ማህበረሰብ በማሳወቅ የሚታደርጉትን የፀረ-ጭቆና ትግል በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ የተቃውሟችሁን ድምፅ የማሰማት ሥራችሁን አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ አጥብቀን እናሳስባለን።
- ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርና ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት እንዲገነባ ለመላው ብሔር ብሔረቦች ፍትህ እኩልነት እና ሀገር ባለቤትነት ለምትታገሉ ተራማጅ የፖለቲካ ኃይላት በሙሉ፡ ከ1987 ዓም ጀምሮ ሀገራችን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በህገመንግስት ደረጃ እውቅና ተሰጥቷቸው ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ስትተዳደር የቆየች ቢሆንም የዎላይታ ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ህገ መንግስታዊ መብት የመጠቀም መብቱን ተነፍጎ ከሌሎች 55 ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር ታጉሮና ታጭቆ በአንድ የቅርጫት ክልል በግድ እንዲተዳደር ተደርጎ ከፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ዳር ተመልካች ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል። ይሁንና ከጥቂት አመታት ወድህ አንዳንድ ብሔሮች በሚፈልጉ መልክ የሚፈልጉትን አደረጃጀት ያገኙ ቢሆንም የዎላይታ ህዝብ ጥያቄ እንደታፈነ የቀጠለ ስለሆነ መላው የዎላይታ ህዝብና ንቅናቄዓችን ከህዝባችን ጎን በመሆን ለጭቁን ህዝቦች መብት፤ ፍትህ፤ እኩል ተጠቃሚነት እና የአገር ባለቤትነት ትግል አጋርነታችሁንና አብሮነታችሁን ከምን ጊዜም በላይ የሚያስፈልገን ታሪካዊ ወቅት ላይ ስለሆነን ከሠላማዊ ትግላችን ጎን በመቆም እየተደረገብን ያለውን ኢ-ህገ መንግስታዊ አሠራር እንዲትቃወሙ በአከብሮት እንጠይቃለን።
ህብረ–ብሄራዊ ፌደራሊዝም ለብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት
ዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)
ዎላይታ ሶዶ ፤ሐምሌ 02 ቀን 2014ዓ.ም