ብድሯን መልሳ ወርቅ ያጠለቀችው ጀግኒት

ከሦስት አመት በፊት በዶሃ የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አቅሙና ብቃቱ እያላት በልምድ ማነስና በጥቃቅን የታክቲክ ስህተቶች የ10ሺ ሜትር ድል ከእጇ ወጣ። ከአመት በፊትም በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በተመሳሳይ ወርቁን ተነጠቀች።

አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ18ኛው የኦሪገን የአለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በታላቅ ተጋድሎ ወርቁን አጠለቀች። የውድድሩን አጨራረስ ከጀግናው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና ኬንያዊው ፖልቴርጋት የሲድኒ ኦሊምፒክ ትንቅንቅ ጋር አመሳስለውታል።

በ10ሺ ሜትር ለራሷም ለኢትዮጵያም የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አስመዝግባለች። ባለፉት አራት ዓመታት አቅሙና ብቃቱ እያላት ማሳካት ያልቻለችውን ወርቅ በማጥለቅም ቁጭቷን ተወጥታለች።

የርቀቱ የአለም ክብረወሰን በእጇ የሚገኘው ለተሰንበት ባለፈው የአለም ቻምፒዮና እንዲሁም ኦሊምፒክ በርቀቱ ወርቁን ያጣችው በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሃሰን ነበር። ለሶስተኛ ጊዜ ይህ ታሪክ የሚደገምበት እድል ሰፊ ነበር።

ይሁን እንጂ ለተሰንበት ካለፉት ስህተቶች ተምራ የጎደላትን የአጨራረስ ችግር አስተካክላ ወደ ቻምፒዮኖቹ አለም ብቅ ብላለች። በአለም ቻምፒዮና ከርቀቱ ፈርጥ እኤአ ከ2017 ከአልማዝ አያና ወዲህ በርቀቱ ወርቅ ያጠለቀች ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አድርጓታል።

በዚህ ውድድር ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተዳከመ የመጣው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የቡድን ስራ ትልቅ ተስፋ እንዳላት ባስመሰከረችው ወጣት አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ነብስ ዘርቶ ታይቷል። እጅጋየሁ ሜዳሊያ ውስጥ መግባት ባትችልም ከለተሰንበት ጋር በመናበብ ለወርቅ ሜዳሊያው መመዝገብ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥታለች።

ለተሰንበት የርቀቱ አዲሷ ቻምፒዮን የሆነችው 30:09:94 በሆነ ሰአት ነው። በርቀቱ ታሪክ እጅግ አጓጊ የአጨራረስ ፉክክር በታየበት ለተሰንበት ሲፈንንና ኬንያውያን አትሌቶችን ጥርሷን ነክሳ ድል ስታደርግ በርካቶች የውድድሩን አጨራረስ ከጀግናው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና ኬንያዊው ፖልቴርጋት የሲድኒ ኦሊምፒክ ትንቅንቅ ጋር አመሳስለውታል።

ያምሆኖ ያለፈው ቻምፒዮና አሸናፊዋ ሲፈን ያሰበችውን ማሳካት ባልቻለችበት ውድድር የ2015 የርቀቱ ቻምፒዮን ኬንያዊቷ ሄለን ኦቢሪ 30:10:02 በመግባት የብር ሜዳሊያውን ወስዳለች። ሌላኛዋ ኬንያዊት ማርጋሬት ቼሊሞ 30:10:07 በሆነ ሰአት ነሐሱን አጥልቃለች።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: