

የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ ከ44 ሚሊየን 500 ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናቆ ርክክብ ተደረገ።
የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቀን 500 ሺህ ሜትሪክ ክዩብ ውሃ የማመንጨት አቅም እንዳለው ተገልጿል።
በዩኒቨርሲቲ በዳውሮ ታርጫ ካምፓስ የተገነባው የንፁህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ርክክብ መደረጉን በዩኒቨርሲቲው ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የግንባታ ፕሮጀክቶች ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዜግነት ወልደ ሚካኤል ገልጸዋል።

በኮንትራክተርነት የወላይታ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ እና በአማካሪነት የደቡብ ዲዛይን ግንባታና ሱፐርቪዥን ስራዎች ድርጅት ከዩኒቨርሲቲው ጋር ውል በመግባት ለግንባታ ፕሮጀክቱ ተፈጻሚነት የድርሻቸውን ሚና ተወጥተዋል ብለዋል ስራ አስኪያጁ።
በተገባው ውል መሰረት ግንባታው የውሃ መስመር(የቧንቧ) ዝርጋታ፤ መገጣጠሚያ፣ የኤሌክትሮ መካኒካል እቃዎች ተከላ፤ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችና የማከፋፈያ ግንባታ ስራዎችን እንደሚያካትት ነው አቶ ዜግነት የገለጹት።
የፕሮጀክቱ ሥራ በአጠቃላይ 8 ኪ.ሜ የውሃ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ፤ 500ሺ ሜትሪክ ክዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለው የኮንክሪት ማጠራቀሚያ እና የጄኔሬተር ቤት ግንባታን አካቶ እንደሚይዝ ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።
በካምፓሱ የሚስተዋለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ሙሉ በሙሉ ለመፍታት ታስቦ የተገነባው ይህ ፕሮጀክት፤ 44,504,309.71 ብር ተመድቦ ተግባራዊ መደረጉን አቶ ዜግነት ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በዛሬው እለት ርክክብ መደረጉን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በቀን 500 ሺህ ሜትሪክ ክዩብ ውሃ የማመንጨት አቅም እንዳለውም አሳውቀዋል።
ይህ የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት የካምፓሱን የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት በአስተማማኝ ደረጃ ለመፍታት ያስችላል ተብሏል።