1659188097033

የክልል አደረጃጀትን አስመልክቶ በዞን እና በልዩ ወረዳ ምክር ቤቶች እየተሰጠ ላለው በሳል ውሳኔ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ምስጋና አቀረበ

ላለፉት ዓመታት የህዝብ ጥያቄ ሆኖ ሲቀርብ የነበረው የክልል አደረጃጀት ጥያቄ በየደረጃው ያለው ህዝብ ውይይት በማድረግ በምክር ቤት ደረጃ ቀርቦ ውሳኔ እየተሰጠበት ይገኛል።

የአደረጃጀት ጥያቄው የህዝቡን የቆየ አብሮነት፣ ወንድማማችነት፣ መተሳሰብ፣ ብሎም ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮችን በማይጎዳ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን የክልሉ መንግስት በአድናቆት ተመልክቶታል።

ከዚህ ቀደም የክልሉ መንግስት የህዝቡን ራስን በራስ የማስተዳደር ዝንባሌ በማክበር የአደረጃጀት ጥያቄዎች በህዝቦች መካከል ያለውን ብዝሃነት በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ሲሰራ መቆየቱ ይታወሳል።

ሂደቱም በህዝቦች መካከል የነበረው የቆየ መልካም እሴት እንዲጎለብት፣ሰላማዊ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተፈጻሚ እንዲሆን መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶት ሲሰራ ቆይቷል።

መንግስት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ቃል መግባቱ ይታወሳል። ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን ለተፈጻሚነቱም በአንክሮ እየተመለከተ የህዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እንደየ ቅደም ተከተላቸው ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።

ከነዚህ የህዝብ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ እና ጎልቶ የወጣው የአደረጃጀት ጥያቄ መሆኑ እሙን ነው።

አሁን በየደረጃው ባሉ ምክር ቤቶች በሳል ውይይት በማካሔድ ክልሉ የሚታወቅበትን ህብረ ብሔራዊነት ለማስቀጠል ብሎም ከተናጠል ይልቅ በጋራ በመሆን መልማት እንደሚቻል የጋራ አቋም መያዙ በአብነት የሚጠቀስ ነው።

የመንግስት ዋነኛ ተግባሩ የህዝብ ፍላጎት በመረዳት ምላሽ መስጠት ነው።በእርግጥ ሁሉም ችግሮቻችን እና ፍላጎቶቻችንን በአንድ ጀንበር ይፈታሉ ማለት አይደለም እንደ ሀገር ያሉብን ችግሮች አያሌ ናቸው።በሌላ በኩል ኢኮኖሚያችን ሲያድግ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚያግደን ነገር አይኖርም።

የክልል አደረጃጀት ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል።

በፈተና ውስጥ እያለፍን የጋራ ችግሮቻችንን በጋራ መፍታት ይኖርብናል።በመሆኑም የህዝባችንን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ በማስመልከት በምክር ቤቶች ደረጃ ውይይት በማካሔድ የቀረበውን አማራጭ ፍላጎት አስመልክቶ የክልሉ መንግስት በድጋሚ ምስጋና ማቅረብ ይወዳል ።