gam

የግል ፍላጎታቸውን ለማሟላት የዞኑን ገጽታ በማበላሸት የትርምስ ቀጠና ለማድረግ በሚጥሩ አካላት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ የጋሞ ዞን አስተዳደር ገለጸ።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እና ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አንዳንድ የግል ፍላጎታቸውን ለሟሟላት የሚሹ አካላት የዞኑን ገፅታ በማበላሸት የትርምስ ቀጠና ለማድረግ እየሰሩ እንደሚገኝ የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው የዞኑ መንግስት የአከባቢውን ሰላም ለማደፍረስ በሚጥሩ አካላት ላይ ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት የፀጥታ አካላት እና ሠላም ወዳድ የሆነው የዞኑ ሕዝብ ተቀናጅተው በመስራታቸው የዞኑ ሠላም ተጠብቆ መቆየቱን ተናግረው የዞኑን የሠላም አምባሳደርነት ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በ2014 በጀት ዓመት በበልግ እርሻ ወቅት በተከሰተ የዝናብ እጥረት ከ35 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የሚገኝ ሰብል መውደሙ የተገለፀ ሲሆን ተጎጂ አርሶ አደሮችን በመለየት ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ከህገ ወጥ የመሬት ወረራ ጋር ተያይዞ በተለይ በደጋማ አከባቢዎች የወል መሬቶች ለግለሰብ የሚተላለፉበት ሂደት በመኖሩ የሚመለከታቸው አካላት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱም ይደረጋል።

የተማሪዎች ውጤታማነትን ለማሳደግ የትምህርት ቁሳቁስ ግብዓት ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ግብዓት የማሟላት ስራ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ተመልክቷል።

በዞኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የሆኑ መንገዶችና ድልድዮችን በጥናት በመለየት ከክልሉ ገጠር መንገድና ከዞኑ መንግስት ጋር ለመስራት መታቀዱም ተገልጿል።

ፈውስን መሠረት ያደረገ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ለጤና ተቋማት የህክምና ግብዓት የማሟላት ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ተጨማሪ የጤና ተቋም ግንባታ የሚያስፈልጋቸው አከባቢዎችን በጥናት በመለየት ምላሽ እንደሚሰጥም ተጠቁሟል።

ከኮንትሮባንድና ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ጋር ተያይዞ ለህገ-ወጦች ከለላ የሚሰጡ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን ከተግባራቸው እንዲታቀቡም ይደረጋል ብለዋል።

በዞኑ ገረሴ፣ ዋጫ፣ ሰላምበር ከተማ የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመቅረፍ በዕቅድ ተይዞ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆን የጨንቻ እና የዘፍኔ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እንዲጠናቀቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እየተደረገ እንደሚገኝም ተመልክቷል ።

የዞኑ አስተዳደር የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የ2015 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል ስል የጋሞ ዞን መ/ኮሚዩኒኬሽን ዘግቧል።