

በቅርቡ ለአንባቢያን የሚደርሰው “ዎላይታ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ትኩረቱ ምኑ ላይ ነው ? ደራሲው ስለመፀሐፉ ምን አስተያየት ሰጡ?
የ”ለምለሚቷ ዎላይታ” የሚል መጽሐፍ ደራሲ እና የዚሁ መጽሐፍ ደራሲ አባት አብርሃም ባባንቶ ባላ ናቸው። አቶ አብርሃም ባባንቶ ለዎላይቱማ የነበረው እልህ እና ቁጭት ከፍተኛ ነበር፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ሰለዎላይታ ባህል ታሪክ ማንነት በድፍረት የመግለጽና የመሞገት ባህሪው ወዳጆቹ ሁሌም የምኮሩበት ነበሩ።
የዚህ መጽሐፍ ደራሲ አማኤል አብርሃም ባባንቶ የዎላይታ ሕዝብ ታሪክና ባህል በተለያዩ መንገዶች ባካበቱት ከፍተኛ ልምድ ከኢትዮጵያ የዘመናዊ መንግስት ምስረታ ሂደት ጋር በማቀናጀት ያቀረቡ በመሆኑ በአፃፃፋቸው ለየት ያለ አቀራረብ እንደተጠቀሙ መፃፉን የተመለከቱ ምሁራን አስተያየት ሰጥተዋል።
ደራሲው ለትውልድ አካባቢው ልማት ለሚሰራውና ለረዥም ጊዜ በቦርድ አመራርነት እንዲሁም አባልነት ለመራው የዎላይታ ልማት ማህበር (ዎልማ) መጠናከር ይተጋል፤ ይደግፋልም፡፡ ከዚህ “ዎላይታ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ሽያጭ ከሚገኘው ገቢ ላይም በተለያዬ መልኩ ለአካባቢው ልማት ለማዋል ለራሱ ቃል ገብተዋል፡፡
ከመጽሐፉ የተወሰደ
“ወቅቱ የካራማራን የድል በዓል ለማክበር ዝግጅት የሚደረግበት ነበር በ1969 ዓ.ም። ለበዓሉ ዝግጅት የሥነ-ጽሑፍ ኮሚቴ አባል ሆኜ በዎላይታ አውራጃ በተመረጥኩ ጊዜ የጥንቱን የዎላይታ ታሪካዊ አመጣጠና ባህል በጽሑፍ ያቆየ ሰው ስላልነበረ በገጠመኝ ችግር እኔም ለሚቀጥለው ትውልድ ይህንኑ በፅሑፍ ባላስተላልፍ የበለጠ ችግር እንደሚገጥመ ተገነዘብኩ።
በዚህ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ሰሪው ሠፊ ህዝብ ይቅርና እንስሳት እንኳን የትውልድ አመጣጣችውና ጊዜያቸው ተመዝግቦ በሚቆይበት በቴክኖሎጂ ዘመን የዎላይታ ብሔር ታሪክ አባል ማድረጉና ከቀሩት የኢትዮጵያ ወገኑ ጋር እንዳይተዋወቅ ማድረጉ የወደቀው የቡርዡዋ ስርዓትና አስተሳሰብ እንጂ የተራማጅ ስርዓት አመለካከት አለመሆኑን በመረዳት ይህችን አጭር የጥቆማ ጽሑፍ አብዮቱ በሰጠኝ ነፃነት ተንተርሼ ለማዘጋጀት በቅቻለው።
በማጠቃለያውም፤- አስጀምሮ ላስፈፀመኝ ፈጣሪዬ እጅግ የላቀ ነው ምስጋናዬ አሻሽዬ ለመጻፍ ነው ዓላማዬ ለዚያው እንዲያበቃኝ ነው “ልመናዬ” በማለት የቋጨው የለምለሚቷ ዎላይታ መጽሐፍ ደራሲ እና የዚሁ መጽሐፍ ደራሲ አባት አብርሃም ባባንቶ ባላ ነው።
“አባቴ አብርሃም ባባንቶ ለዎላይቱማ የነበረው እልህ እና ቁጭት ከፍተኛ ነበር፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ ሰለዎላይታ ባህል ታሪክ ማንነት በድፍረት የመግለጽና የመሞገት ባህሪው ወዳጆቹ ሁሌም የምኮሩበት ነው።
ከዚሁ አብሮት ካደገው ባህሪይ በመነሳትም ለመነሻ ሊያገለግል እንደሚችል አስቦ ያዘጋጀውን የዎላይታን አጭር ታሪክ አዘጋጅቶ ለህትመት ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባመራበት በ1971 ዓ.ም የገጠመው ፈተና ብዙ ነው።
በመጀመሪያ በቅድመ ምርመራ (Sencership) ማለፍ ነበረበትና ለመርማሪዎች አስረከበ። በወቅቱ የነበሩትን ሥርዓቶች ጠጋግኖ ለማስቀጠል የተቀመጡ ባለሟሎች ስለነበሩ ሥርዓቱን ሊነኩ ይችላሉ ያሏቸውን በሙሉ ሰርዘውና ደልዘው እነሱ በሚፈልጉት ቃላትና ሐሰብ በመተካት እንደገና አጽፈው እንዲያመጣ ይሰጡታል።
በጉዳዩ እጅጉን የተከፋ ቢሆንም ከመቅረት መታተም እንደሚሻል በመገንዘብና ቢችል ራሱ ካልሆነም ቀጣዩ ትውልድ የጎደለውን እየሞላ ታሪኩን፣ ባህሉንና ማንነቱን አስጠብቆ እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት ስላሳደረ የጽሑፉ መርማሪዎች ባሉት መሠረት አሰናድቶ በተጨማሪም ምልጃ በመስጠት አስፈቅዶ ለምለሚቷ ዎላይታን በማሳተም ለዎላይታ ብሔረሰብ ባህል፣ ታሪክና ማንነት ድርሻውን አኑሮ አልፏል”።
በዚህ መጽሐፍ ደራሲ ውስጥም የነበረውን የተቆርቋሪነት ስሜት አውርሶት በመሄዱ ምክንያት አሻሽሎ የመፃፍ ህልሙ እነሆ በልጁ እውን ሆኗል።
ባፉት 28 ዓመታት በዎላይታ ህዝብ ስም በመመረጥ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለ15 ዓመታት፤ በሚኒስትር ዴኤታነት እና በተለያዩ የህዝብ ኃላፊነት ደረጃዎች ባገለገልኩባቸው ወቅቶች ሁሉ የዎላይታ ህዝብ ጉዳይ በውስጤ ሸክም ሆኖ ቆይቷል።
በመሆኑም የዎላይታን ብሔር እውነተኛ ታሪክ፣ ማንነትና አኩሪ ባህሉን፤ በዘመናት ሲደርስበት ከነበረው መዋቅራዊ የጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ የከፈላቸውን መስዋዕትነቶች የመረጃ ዘመን የፈጠረውን የቴክኖሎጂው ዕድል በመጠቀም በማዘጋጀት የበኩሌን ድርሻ ለመወጣት ችያለሁ ብዬ አምናለሁ።
የዚህ መጽሐፍ ዋና ዓላማ ያለፈውን ታሪክ እያወራን ለመቆዘም ከቶውንም ሊሆን አይችለም። አይገባውምም። ነገር ግን ደግሞ በተዛባ እና ትክክለኛ ማንነትን በመድፈቅ የሌላን ማንነት ለማላበስ ሲደረግ ከነበረው አስከፊ እና ሥርዓታዊ አድሎ ሁላችንም ትምህርት ወስደን ያሳለፍነውን መንገድ ለማሞካሸትም ሆነ ለማውገዝ በትክክለኛ መረጃ ላይ መመስረት አስፈላጊ መሆኑን በማመን ነው።
በመጽሐፉ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አካላት የተፃፉ ጽሐፎችን እንደማጣቀሻነት የተጠቀምኩ ቢሆንም በተቻለ መጠን በአፃፃፉ እና በአደረጃጀት ለየት እንዲል እና በአንድ ማዕድ በዎፍ በረር ቅኝት ስለዎላይታ ገጽታ የተማላ ግንዛቤ ለመስጠት ያግዛል ብዬ አምናለሁ” ፡፡ ከመፃፉ የተወሰደ

የመፅሐፉ ደራሲ አቶ አማኑኤል አብራሃም በኢትዮጵያ እስከ ሚኒስቴር ደኤታነት ጨምሮ በተለያዩ በመንግሥት ከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉ፤ በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ሀገራቸውን እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ በፊትም የተለያዩ መፅሃፍትን በመፃፍ ልምድ ያካበቱ ናቸው።

በዎላይታ ታሪክ ላይ በርካታ የጥናትና ምርምር መጽሐፍት እየታተሙ ቢሆንም ይህ መጽሐፍ ግን በመረጃ ሀብታምነቱ በአደረጃጀቱና በይዘቱ ለየት ያለና የዎላይታ ታሪክና ችግሮችን በጣም ገላጭ በሆነ መንገድ በበቂ ማስረጃ በማስደገፍ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ያስቀመጠ ረጅም ጊዜ ተወስዶ የተፃፈ መሆኑን አርካ አቦታ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ ረዳት ኘሮፌሰር መስክሮለታል።
ይህ የ “ዎላይታ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ በከፍተኛ ጥራትና ደረጃ ለአንባቢያን በበቂ ሁኔታ ለማድረስ ህትመት ላይ ሲሆን በቅርቡ በይፋ እንደሚደርስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
እርስዎ ይህን መጽሐፍ ሲገዙ ለዎላይታ ልማት ማህበር 30.00 ብር አበረከቱ ማለት ነው፡፡ ለዞኑ ልማት ስላሳዩት አጋርነት ደራሲው ከልብ ያመሰግናል፡፡