
የህዝብ ተመራጮች የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የስራ እንቅስቃሴ በመከታተልና በመደገፍ ለወከላቸው ህዝብ ተጠቃሚነት ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ አሳሰቡ
የክልሉ የህዝብ ተመራጮችና የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የጋራ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የደቡብ ክልል የፓርላማ ተወካዮች፣ የክልሉ አመራሮች፣ የዞንና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችና አፈ ጉባኤዎች እንዲሁም የክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች ከዚህ ቀደም በህዝብ ተነስተው በነበሩ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲሁም የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በሀዋሳ የጋራ ውይይት አካሂደዋል።
በጋራ መድረኩ ላይ ከፌደራልና ከክልል የህዝብ ተመራጮች ባሻገር ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የመድረኩ ዋነኛ አላማ ከዚህ በፊት ከህዝቡ የተነሱ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና የጸጥታ ሁኔታዎች ያሉበትን ደረጃ መገምገምና መረጃ መለዋወጥ እንደሆነ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ተናግረዋል ።

ተመሳሳይ የህዝብ ተመራጮችና የሴክተር ሃላፊዎች የጋራ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅትና በተከታታይ እንደሚሰራም ወ/ሮ ፋጤ አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ እንደተጠቆመው የክልሉ ነዋሪዎችና በየደረጃው ያሉ የህዝብ ተወካዮች በተለያዩ መድረኮች ላይ በመሰረተ ልማቶች ፍትሃዊ ስርጭት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ የኑሮ ውድነት፣ በግብርና ግብኣቶች አቅርቦትና ዋጋ መናር፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በውሃ ተቋማት ብልሽት፣ በመስኖና መንገዶች ተደራሽነትና ግንባታ መጓተት፣ በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
በጤናው መስክ የተቋማት ግንባታ መጓተት፣ የሆስፒታሎች ማስፋፊያ፣ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች እጥረት፣የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የሚታየው የእናቶች ጤና አገልግሎትና ክትባት ሽፋን ጉዳዮች በስፋት መነሳታቸው የተጠቆመ ሲሆን በትምህርት ዘርፍ የጥራት መጓደል፣ የመምህራንና የግብኣት እጥረት፣ የስነ ዘዴና የተማሪዎች ስነ ምግባር ግንባታ ሂደት ልዩ ትኩረት እንዲሰጣቸው ህብረተሰቡ በየደረጃው ጥያቄዎችን ማንሳቱን የህዝብ ተወካዮቹ አስታውቀዋል።
በስራ እድል ፈጠራ ረገድ በስራ አጥ ልየታና ስምሪት፣በምርት ማሳያና መሸጫ ህንጻዎች መጓተት፣ በክላስተር ማዕከላት ወደ ተሟላ አገልግሎት አለመግባት፣ በብድር አቅርቦትና አመላለስ በኩልም የተቀናጀ ትኩረትን የሚሹ ጉዳዮች አሉ ብሎ ህዝቡ በግልጽ ማስቀመጡን የምክር ቤት አባላቱ ጠቁመዋል ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአርብቶ አደር አካባቢዎች የሚታዩ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ፣የሆስቴሎች አናሳነት እና የመስኖ ተቋማት ግንባታ ለረጅም ጊዜያት መጓተት የህዝብ ቅሬታ ምንጮች እንደነበሩ ተወስቷል።
በሌላ በኩልም በሰላምና ጸጥታ በኩል የህዝቦችን ደህንነት ስጋት ውስጥ ላስገቡ ግጭቶች፣ ዝርፊያዎች፣ ትንኮሳዎችና የመሰረተ ልማት ውድመቶች ዘላቂ መፍትሄ መበጀት እንዳለበት ህዝቡ የሚመለከታቸውን አካላት መጠየቁም በዚሁ የጋራ መድረክ ላይ ተነስቷል።

የህዝብ ተመራጮቹ ለእነዚህ የህዝብ ጥያቄዎችና የልማት ፍላጎቶች በተሰጠው ተግባራዊ ምላሽና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ማብራሪያዎችንና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን የየዘርፉ የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚሁ መሰረትም በክልሉ የበጀት አቅምን መሰረት ባደረገ መልኩ በተለይ በተጓተቱና የህዝብ ቅሬታ ምንጭ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ አመርቂ ውጤት መገኘቱን የቢሮ ሃላፊዎች አብራርተዋል ።
በዚህ እንቅስቃሴ ለአመታት ሳይጠናቀቁ የቆዩ ተቋማትን ወደ አገልግሎት ማስገባት መቻሉንም ያነሱ ሲሆን ካለው የበጀት ውስንነት አኳያ አሁንም ቅድሚያ የሚሹ ጉዳዮች ተለይው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ የህዝብ ተመራጮች የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችን የስራ እንቅስቃሴ በመከታተልና በመደገፍ ለወከላቸው ህዝብ ተጠቃሚነት ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ምክር ቤቶች በህዝብ ተጠቃሚነት ዙሪያ ከአመራሩ ጋር የአስተሳሰብ አንድነት ፈጥረው አፈጻጸሞችን መከታተል ብቻ ሳይሆን በተቀናጀ መንገድ መደገፍና ለህዝብ ጥያቄዎች መመለስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ለዚህ ስኬት ደግሞ የሰላም መረጋገጥ ቁልፉ ጉዳይ በመሆኑ ቅንታዊ ርብርብ ይጠይቃል ሲሉም ጠቁመዋል ።ተቀራርቦ መወያየት፣መደማመጥና መቀናጀት ያስፈልጋል ሲሉም ተደምጠዋል።
የልማት ፍላጎትና የኢኮኖሚ አቅም መጣጣም አለበት ያሉት አቶ እርስቱ ባለፉት ሁለት አመታት 30 ቢሊየን ብር የሚፈልጉ የተጓተቱ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ ጠቁመው ክልሉ የነበረው በጀት ግን 3 ቢሊየን ብቻ እንደነበር አስረድተዋል።
ያም ሆኖ የጸጥታ ቀውሱን ተቋቁሞ ወሳኝ ፕሮጀክቶችን ለስኬት ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል ።በተለይ የበጀት አቅም ውስንነት፣ የግንባታ ግብኣቶች ዋጋ በየጊዜው መናር እና የማሽነሪ አቅም ትልቅ ፈተና ነበር ሲሉም አክለዋል።
ወቅቱ የህዝብ ተወካዮችና በየደረጃው ያሉ ተቋማትና አመራሮች ከምንጊዜውም በላይ ተቀናጅተውና ተቀራርበው የሚሰሩበት በመሆኑ ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ እርስቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የክልሉ መንግስት በቀጣይ የህዝቡን የጋራ እሴቶች ለማጎልበትና የአደረጃጀት ጥያቄ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
የጋራ የውይይት መድረኩ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንና ቁልፍ ተግባራትን በማስቀመጥ ይጠናቀቃል ስል የክልሉ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።