አቶ ገብረሚካኤል ኩኬ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በቀድሞ ዎላይታ አውራጃ በዳሞት ጋሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ሊቢቃ በሚባልበት አካባቢ ነው፡፡ ስለ ትውልድ ጊዜያቸው ሲናገሩ በወቅቱ ጣሊያን ዎላይታ ሶዶ ከተማ የገባ ጊዜ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ ጣሊያን አዲስ አበባ የገባው በ1928 ዓ.ም ሲሆን ወደ ዎላይታ ሶዶ ደግሞ በዓመቱ ነው። ይህም በ1929 ዓ.ም እንደሆነ ከተነገራቸው መረጃ እንደተረዱ አጫውተውናል፡፡

ዘንድሮ 85 ዓመታቸው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ገብረሚካኤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት በወላይታ ሶዶ ሊጋባ በየነ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሊጋባ በየነ “አባ ሰብስብ” ተብሎ ከመሰየሙ በፊት ሶዶ ትምህርት ቤት ይባል በነበረበት ወቅት እንደሆነ በማስታወስ ይናገራሉ፡፡ የህይወት ታሪካቸውን ይቀጥላሉ፡ – “በወቅቱ እስከ 3ኛ ክፍል ድረስ እዛው ተማርኩኝ፡፡

ሶስተኛ ክፍል ትምህርቴን እንዳጠናቀኩኝ ሊጋባ በየነ “አባ ሰብስብ ትምህርት ቤት” ተብሎ በጡብ ድንጋይ ፎቅ በጣሊያን ኮንትራክተሮች ሲሰራ በወቅቱ ጉልበት ያላቸው ወጣቶች ድንጋይ በማቃበል ተሳትፎ ሲያደርጉ፣ እኔም ውሃና ድንጋይ በማቀበል የራሴን አስተዋጽኦ አበርክቻለሁ፡፡ “የትምህርት ቤቱ ህንፃ የተገነባው በ1946 ዓ.ም ነው፡፡ እኔም እድለኛ በመሆን አሻራዬን ባሳረፍኩበት ትምህርት ቤት በ1947 ዓ.ም የ4ተኛ ክፍል ትምህርቴን ተማርኩኝ፡፡ “እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ እዛው ቀጠልኩኝ፡፡

የ8ኛ ክፍል የሚኒስትሪ ፈተና ተፈትኜ ጥሩ ውጤት በማምጣት ከ8ኛ ክፍል መምህራን ማሰልጠኛ አዲስ አበባ ኮከበ አፅበሃ ትምህርት ቤት በመግባት ለአራት ተከታታይ ዓመታት ተምሬ ተመረቅኩኝ፡፡ “በሁለገብ ትምህርት በ1954ዓ.ም ተመርቄ ከትምህርት ሚኒስቴር እጣ በማውጣት ከፋ ክፍለ ሀገር ሄድኩኝ፡፡ “በዓመቱ ከመሰል ጓደኞቼ ጋር ወደ ከፋ ክፍለ ሀገር በመሄድ ሪፖርት ስናደርግ እዚያው ሌላ እጣ ሲወጣ ከፋ አውራጃ ዋና ከተማ ቦንጋ ደረሰኝ፡፡ “በወቅቱ ትራንስፖርት ስላልነበረ በበቅሎ ወደ ቦንጋ ከገባን በኋላ ለትምህርት ጽህፈት ቤት ደብዳቤ በመስጠት ምደባ ይሰጣችኋል ጠብቁ ተባልን፡፡ “ከሶስት ቀናት በኋላ የ8ኛ ክፍል ህብረተሰብ ሳይንስ እንዳስተምር ተሰጥቶኝ ለሁለት ዓመታት ያህል ካስተማርኩ በኋላ በዓመቱ ወደ ዋካ ተዛወርኩኝ፡፡

በወቅቱ ተማሪዎች እጅግ ፈጣንና ታታሪ እንደነበሩ አስረድተው “በትምህርቱም ይሁን ለመምህራን ጥሩ አክብሮት ያላቸው ነበሩ፡፡ ኋላ በቀጣይ ዓመት ሶስተኛ ክፍል እንዳስተምር ተደረኩኝ” ብለዋል፡፡ ስለ ቦንጋ ሲያወሱ “ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ቦንጋን ብለቅም የማይረሳ ትዝታ ነበር። ቦንጋ ላይ ኑሮ በጣም ርካሽ ነበረኝ፡፡ አየሩም ቀዝቃዛና ነፋሻማ ለኑሮ እና ለጤና እጅግ ተስማሚ ነበር፡፡

ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር በተገናኘም፡- “በጣም ጎበዝ ተማሪዎችን ያፈራሁበት ትምህርት ቤት በመሆኑ እጅግ ብዙ ትውስታዎች አሉኝ” ያሉት አቶ ገብረሚካኤል “ዛሬ ላይ ያስተማርኳቸው ተማሪዎች የህዋ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑትን ሳስታውስ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡

እራሴን ተክቻለሁ ማለት እችላለሁ” ብለዋል፡፡ ባለታሪካችን ከቦንጋ ቆይታ በኋላ ወደ ዋካ ተዛውረው መምጣታቸውን አስታውሰው በደረሱበት ሁሉ ተማሪዎቻቸውን እንደሚጠይቁአቸው አጫውተውናል፡፡ “በዋካም አንድ ዓመት ከቆየሁኝ በኋላ የሲዳማ ጠቅላይ ግዛት ክብረመንግስት በሚባልበት አካባቢ ዝውውሬን ጨርሼ ገባሁ፡፡ “በክብረመንግስትም አንድ ዓመት ካስተማርኩኝ በኋላ ወደ ወላይታ ሶዶ ተዛውሬ በአሮጌ አራዳ ሶዶ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት በሚባልበት ሁለት ዓመት አስተማርኩ፡፡

ኋላ ቦዲቲ ቤተሰቦቼ ስለነበሩ በ1962 ዓ.ም በዝውውር ገባሁኝ ” ብለዋል፡፡ አቶ ገብረሚካኤል እንደሚናገሩት የመምህርነት ስራ አብዛኛው በመንቀሳቀስ የሚሰራ በመሆኑ ከሰባት ዓመት የቦዲቲ ቆይታ በኋላ ለአድቫንስ ዲፕሎማ ኋላም ለድግሪ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ትምህርታቸውን ተከታትለው ተመርቀዋል፡፡ ከምረቃ በኋላ እዚያው አዲስ አበባ ትምህርት ሚኒስቴር ማስታወቂያ ሲያወጣ በመወዳደር በ1974 ዓ.ም የትምህርት መገናኛ ዘዴዎች ፕሮግራም ትምህርት በሬድዮ በወላይትኛ ቋንቋ ይቀጠራሉ፡፡

ማስታወቂያውም በወቅቱ ወላይትኛ ቋንቋ የሚያዘጋጅ ተብሎ ስለወጣ ያዘጋጁ የነበሩት በወላይትኛ ቋንቋ ነበር፡፡ የትምህርት በሬድዮ ፕሮግራም በማዘጋጀት ለ6 ተከታታይ ዓመታት እንደሰሩ አጫውተውናል፡፡ “በወቅቱ ለጎልማሶች ግብርና፣ ጤናና ፖለቲካ ነክ ጉዳዮችን በማዘጋጀት አስተላልፍ ነበር” የሚሉት ባለታሪካችን “በዚያም ውጤታማ ነበርኩኝ፡፡

በብዙዎች ዘንድ ታዋቂ እንድሆን መነሻና መንደርደሪያ ሆኖኛልም” ብለዋል፡፡ “ከ 6 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሌላ ማስታወቂያ በወጣው መሰረት በቴሌቪዥን የሳይንስ ትምህርት ለማዘጋጀት ተወዳድሬ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ በመሆን ጡረታ እስከወጣሁት 1978 ዓ.ም ለ10 ዓመታት ሰርቻለሁ” ሲሉ በጋዜጠኝነት ያሳለፉትን ህይወት ያጋራሉ፡፡ “ጡረታ ከወጣሁኝ ዛሬ 25 ዓመታትን አስቆጥሬያለሁ፡፡

ከጡረታ በኋላ በወላይታ ልማት ማህበር ለአንድ ዓመት ከሰራሁ በኋላ በአካባቢው ባለው የሬድዮ ፕሮግራም በእኔ መሪነት በወላይትኛ ቋንቋ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን እንዳዘጋጅ ኃላፊነት ተሰቶኝ ስለነበር ይህንኑ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡ “በዚህም መሰረት የትምህርት በሬድዮን ቅዳሜ፣ እሁድ እና ክረምትን ጨምሮ ሌላ 10 ተከታታይ ዓመታት አስተባብሬአለሁ” ሲሉ ስለሰሩት ስራ ያወሳሉ፡፡

በወቅቱ የልማት ማህበሩና ፖለቲካ ድርጅቱ /ወጋጎዳ/ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋና ዳውሮ የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በአርባ ምንጭ በርካታ ስራዎችን ከማደራጀት ጀምሮ በውጤታማነት መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡ “ጡረታ ከወጣሁኝ በኋላም ያለ ስራ በከተማ መዞርና መቀመጥን አልወድም ነበር። ሌላ አማራጮችን ሳፈላልግና ሳቅድ ከቆየሁ በኋላ የወላይታ ባህላዊ ዘፈኖችን ለምን አላሰባስብም በማለት አሰብኩኝ፡፡ “ዕቅዴም ተሳክቶ ለአንድ ዓመት በራሴ ተነሳሽነት 12 ዘፈኖችን የያዘ ካሴት አዘጋጅቼ ድምፃዊ ፈልጋችሁ አሰሩ በማለት ሰጠሁኝ።

በወቅቱ በወላይታ ሶዶ አንድ ሙዚቃ ቤት ብቻ ነበር፡፡ እርሱም ‘ካራማራ ሙዚቃ ቤት’ ይባል ነበር፡፡ እስከ ዛሬም አለ፡፡ “የሙዚቃ ቤቱ ባለቤትም የእኔ ተማሪ ስለነበር ሥራው እንደሚያዋጣው ካየ ወዲህ ድምፃዊ አፈላልጎ ካለማመድኩት በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ ካሴቱን አሰራው፡፡ በወቅቱ እኔ ግን ምንም ጥቅም አላገኘሁበትም ነበር” “በወቅቱ ዘፈኑ ስለተወደደ የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት ጥሩ ገቢ አግኝቷል፡፡ “በ1992ዓ.ም ካሴቱ ሲወጣ የማንኛውም የእምነት ተከታዮች ወደውት ነበር የገዙት፡፡ “ወጋጎዳ ታሪካዊና ባህላዊ ስያሜ አልነበረውም፡፡

ከአራቱ ቋንቋዎች የመጀመሪያዎችን ፊደላት በመውሰድ ነበር ምህፃረ ቃሉን የተጠቀምነው፡፡ ምንም ባስተባብር እንኳን እጅግ ተቋዋሚ ነበርኩ። ምክንያቱም እነዚህ አራቱ ቋንቋዎች መቀራረቡ ቢኖራቸው እንኳን ቀበልኛው የተለያየ ነው፡፡ ምንም አይገናኝም ይላሉ ፡፡ ስለግል ህይወታቸው ሲናገሩ “የዘመድ ልጆችን አሳድጌ ለወግ ማዕረግ አድርሻለሁ” የሚሉት ባለታሪካችን “የአብራኬ ክፋይ ቦንጋ በነበርኩበት ወቅት ከጋብቻ ውጪ የወለድኩት አንድ ልጅ አለኝ፡፡ ብዙም የአባትና የልጅ ግንኙነት እና ቀረቤታ ሳይኖረን ተለያየን፡፡

በአሁኑ ወቅት የት እንደደረሰም አላውቅም” ብለዋል፡፡ “በወቅቱም እራሴን በስራ ከመወጠርና ስራ ከመፍጠር እና በበጎነት ከማሳድግ ውጪ ወደ ትዳር አላዘነበልኩም፡፡ ለራሴ ሳይሆን አብዛኛውን ጊዜ ለሰዎች ኖሬአለሁኝ” ይላሉ ባለታሪካችን አቶ ገብረሚካኤል ኩኬ ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ስሉ ከደቡብ ንጋት ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: