1662736977531

አርቲስት ካሙዙ ካሳ አንጋፋ የሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፋበት “ስናብር ስናምር” የተሰኘው የሙዚቃ አልበም ለመከላከያ ሠራዊት ተበረከተ።

የሙዚቃ ባለሙያዎቹን ወክሎ አልበሙን ያስረከበው አርቲስት ካሙዙ ካሳ የአልበሙ ስጦታ በሀገር አቀረፍ ደረጃ ጳጉሜ 5 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከበረውን የአንድነት ቀን ምክንያት በማድረግ መሆኑን ገልጿል።

የሙዚቃ አልበሙ በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተሰሩ አንድነት እና አብሮነትን የሚሰብኩ እና የበዓል ሙዚቃዎች የተካተተበት ነው።

የሙዚቃ አልበሙን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብርሀም በላይ አንድነት ድክመትን እንደሚያሸንፍ ገልጸው የቋንቋ እና የጾታ ስብጥር ያለበት የሙዚቃ አልበሙ ዘመን ተሻጋሪ እና የኢትዮጵያን መጻኢ ተስፋ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በተደረጉት ዘመቻዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጸው ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሙያ ዘርፍ ለሰላም ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከሙዚቃ አልበሙ ስድስቱ ሙዚቃዎች ክሊፕ የተሰራላቸው ሲሆን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሀም በላይ አልበሙ በተለያዩ ሚዲያዎች ለእይታ እንዲበቃ ለመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ለአቶ ከበደ ዴሲሳ አበርክተዋል።