ስለዘመናዊው ኢ-ሲም ከማውራታችን በፊት ሁላችንም ስለምናውቀው ሲም ካርድ ትንሽ እንበል።

ሲም አሊያም በእንግሊዝኛው Subscriber Identification Module ተብሎ የሚጠራው በመጠኑ ትንሽ የሆነ ቁራጭ ፕላስቲክ ነው።

ይህ ስልካችን በምንቀይርበት ወቅት ከስልካችን የምናስወጣውና የምናስገባው ወይም በሚጠፋበት ወቅት የምንተካው ቁስ፣ የተጠቃሚውን ዝርዝር መረጃ ወደ ኔትዎርክ የሚያስተላልፍና የያዝነውን ስልክ ትክክለኛነት የሚያረጋግጥ ነው።

ሲም ካርድ የስልክ ቁጥር ከመያዝ አንስቶ ሌሎች መረጃዎችን በውስጥ የሚያከማች ሲሆን፣ ስልክ ለመደወልና ለመቀበል እንዲሁም የኢንተርኔት ዳታን ለመጠቀም ያስችለናል።

ሲም ካርዶች እ.ኤ.አ በ1991 መጀመሪያ ከነበራቸው የክሬዲት ካርድ ቅርጽ ካለው መጠን ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ ትንሹ [ሚኒ] መጠን ተሻሽለው መጥተዋል።

በ2003 ማይክሮ ሲም የተሰኘው በቅርፁ ያነሰ ሲም፣ አይፎን 4 ከተሰኘው ምርት ጋር ተያይዞ ነበር የመጣው።

በ2012 ደግሞ ናኖ የተሰኘው በቅርፁ ከሌሎቹ እጅግ ያነሰው ሲም ካርድ ጥቅም ላይ ዋለ።

ኢ-ሲም አሊያም በእንግሊዝኛው ኢምቤድድ ሲም የተሰኘው አዲስ ቴክኖሎጂን የተዋወቀው በፈረንጆቹ 2016 ነው።

ይህ ሲም ከዚህ በፊት እንደነበረው በእጃችን ዳሰን ስልካችን ውስጥ የምናስገባውን ሲም ካርድ የሚያስቀር ሲሆን አገልግሎቱ ግን የተለየ አይደለም።

የፕላስቲክ ካርድን የሚያስቀረው ይህ ቴክኖሎጂ፣ ስማርት ስልኮች ሲመረቱ ተገጥሞ [ኢምቤድድ] የሚመጣ ነው።

ዲጂታል የሆነው ይህ ቴክኖሎጂ ከአንድ ስልክ ወደ ሌላው ተነቅሎ የሚዘዋወር አይደለም።

የዘመናዊ ስልኮች ‘ቦርድ’ ላይ ተገጥሞ የሚመጣው ኢ-ሲም ያከማቻቸውን መረጃዎች ሰርዞ አዲስ ማከማቸት ይቻላል።

ከአንድ የኔትዎርክ አቅራቢ ወደ ሌላኛው የኔትዎርክ አቅራቢ ያለዎትን ሲም ከስልክዎ ሳያወጡ መቀየር ይችላሉ ማለት ነው።

አልፎም ተጨማሪ የኔትዎርክ አቅራቢ መጠቀም እንዲችሉ ያደርጋል። ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና ሳፋሪኮምን ኔትዎርኮችን በአንድ ጊዜ ያለ ሲም ካርድ መጠቀም ይችላሉ።

የሶፍትዌር ኢንጂነሩ ወጣት ሮቤራ ግርማ ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነውን ኢ-ሲም መጠቀም ከጀመሩ ደንበኞች አንዱ ነው።

ሮቤራ የኢ-ሲም አገልግሎትን ለረዥም ጊዜ በጉጉት እየጠበቀ እንደነበር የሚናገር ሲሆን፣ ኢትዮ-ቴሌኮም ይህን ቴክኖሎጂ ሲያስተዋውቅ በፍጥነት ሄዶ አንደተመዘገበ ይገልጣል።

ሮቤራ የኢ-ሲም ተጠቃሚ ለመሆን የፈለገበት አንደኛው ምክንያት የእጅ ስልክ ስርቆትን ለማስቀረት እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

አሁን ግን በአንድ ስልክ የተለያዩ ኔትዎርክዎችን መጠቀም የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ መጠቀሙ ችግሩን እንደሚያልለት ያምናል።

የትኞቹ ስልኮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ናቸው?

የጋላከሲ ፒክስል ስልኮች ከ2017 ጀምሮ ኢ-ሲም ነበራቸው፤ የአፕል ስልኮች ደግሞ ከ2018 ጀምሮ ኢ-ሲም ይዘው መጥተዋል።

ሳምሰንግ ስልኮች ኢ-ሲም ካርድ ይቀበላሉ። ነገር ግን ሁሉም የሳምሰንግ ምርቶች የዚህ ሲም ካርድ አገልግሎትን ይቀበላሉ ማለት ግን አይደለም።

ዘመናዊ የሚባሉና በቅርብ ጊዜ የተመረቱ ሳምሰንግ ጋላክሲ ስማርት ስልል የኢ-ሲም ካርድ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ኢትዮ ቴሌኮም ይገልጻል።

ለምሳሌ ሳምሰንግ ጋላክሲ ኤስ20 እስከ 22 እንዲሁም ሳምሰንግ ኖት ስልኮች ይህን አገልግሎት ማስተናገድ ይችላሉ።

ሳምሰንግ ጋላክሲ ዜድ ፎልድና ፍሊፕ የተባሉት ታጣፊ ስልኮችም ኢ-ሲም ካርድ ተጠቃሚ ናቸው።

ከዚያ ውጭ የአፕል ምርት የሆኑ አይፎን ስልኮችም ኢትዮጵያ ውስጥ ኢ-ሲም ለመጠቀም እንደሚያስችሉ ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል።

ከአይፎን ኤክስ ጀምሮ እስከ አይፎን 13 ድረስ ያሉ በቅርብ ዓመታት የተመረቱ ስልኮች ካለዎ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

በፈረንጆቹ 2022 የተመረተው አይፎን ኤስኢ 3 ስልክም ኢ-ሲም ይቀበላል።

ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ለገበያ የበቃው አይፎን 14 የዚህ አገልግሎት ተቀባይ መሆኑን ባይገልጥም ይህ ዘመናዊ ስልክ ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ሲመጣ ኢ-ሲም የመጠቀም አቅም እንዳለው ይገመታል።

የዓለም የተንቀሳቃሽ ስልክ ገበያን ከተቆጣጠሩት ሳምሰንግና አይፎን ስልኮች በተጨማሪ ጉግል ፒክስል ስልኮች ሲም ይወስዳሉ።

ኦፖ የተሰኘው ቻይና የምታመርተው ስልክም ይህን ቴክኖሎጂ የሚያስጠቅም ቢሆንም፣ ጥቂት የኦፖ ምርቶች ናቸው በኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርክ ተቀባይነት ያላቸው።

ሁዋዌ ፒ40፣ ፒ40 ፕሮና ሁዋዌ ማቴ 40 እንዲሁም አራት ዓይነት የሞቶሮላ ምርቶች በኢትዮ ቴሌኮም ኔትዎርክ ተቀባይነት አግኝተዋል።

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ በመግባት ሥራ የጀመረው ሳፋሪኮም ኢ-ሲም ተግባራዊ ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል።

ጎረቤት አገር ኬንያ በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ሳፋሪኮም፣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ሁሉ ዘመናዊ በሚባሉ ስልኮች አማካይነት የኢ-ሲም ካርድ አገልግሎት ይሰጣል።

የኢ-ሲም ካርድ ጥቅም

አፕል በቅርቡ ለተጠቃሚው ይፋ ያደረገው አይፎን 14 ስልክ ለአሜሪካ ገበያ የሚውለው የሲም ካርድ ማስገቢያ የሌለው አንደሆነ ጠቅሷል።

ይህ የአፕል ውሳኔ በርካታ የኔታዎርክ አቅራቢዎች ኢ-ሲም አገልግሎት እንዲጀምሩ ሊገፋፋቸው ይችላል።

የሲም ካርድ ማስገቢያ የሌለው ስልክ ለገበያ በማቅረብ የመጀመሪያው አፕል ሳይሆን ሞቶሮላ ራዝር ፍሊፕ የተሰኘው ስልክ ነው።

በእንግሊዝኛ አጠራር ኢምቤድድ ሲም የሚባለው ይህ ሲም ካርድ በእጃችን የምንዳስሰው ሲም ካርድ ከምትሰጠው ጥቅም በተጨማሪ የተለያዩ ጥቅሞች አሏት።

ስልክዎ ኢ-ሲም የሚቀበል ከሆነ የሲም ካርድ ማስገበያ ካለው የሁለት ሲም ካርድ ባለቤት መሆን ይችላሉ ማለት ነው።

በኢ-ሲም አማካኝነትም ሁለት ሲም ካርድ መጠቀም ይችላሉ። ስለዚህ አንደኛው የኢ-ሲም ጥቅም በአንድ ስልክ ሁለት ሲም ካርድ እንዲይዙ ማስቻሉ ነው።

ሁለት ሲም ካርድ የሚጎርሱ ቀደምት ስልኮች እንዳሉ ሆነው ኢ-ሲም በሚበቀሉ ስልኮች ግን እስከ አምስት ሲም ካርድ ማስመዝገብ ይችላሉ።

ሌላኛው የኢ-ሲም ካርድ ጥቅም ከአንድ ኔትዎርክ ወደ ሌላ መቀየር ከፈለጉ አዲስ ሲም ካርድ መግዛት ግዴታ አለመሆኑ ነው።

በአንዳንድ አገራት ይህን ለማድረግ ወደ ኔትዎርክ አቅራቢው ስልክ መደወል ግድ ይላል፤ በበይነ መረብ አማካይነትም ኔትዎርክ መቀየር ይቻላል።

ለምሳሌ ከሳፋሪኮም ወደ ኢትዮ ቴሌኮም መቀየር ከፈለጉ አዲስ ሲም መግዛት ሳይጠበቅብዎ ማዛወር ይችላሉ።

በተለይ ደግሞ ከአገር አገር ለሚጓጓዙ ሰዎች መርፌ ፈልጎ ሲም ካርድ ጎርጉሮ አውጥቶ ሌላ ከመሰካት ይገላግላቸዋል።

ከደኅንነት አንፃር ደግሞ መንታፊዎች ሲም ካርድዎን አውጥተው እንዳይበዘብዙት ይከላከላል።

የኢ-ሲም ካርድ አሉታዊ ጎን

ኢ-ሲም የተለያዩ ጥቅሞች ቢኖሩትም ጉዳቶችም አሉት።

ለምሳሌ ስልክዎ ቢበላሽ እንደ ቀደመው ጊዜ አንድን ሲም ካርድ አውጥተው ወደ ሌላ ስልክ አስገብተው መጠቀም አይችሉም።

ፎርብስ የተሰኘው መፅሔት በቴክኖሎጂ ገፁ እንዳሰፈረው አንደኛው የኢ-ሲም ጉዳት በቀላሉ ‘ትራክ’ ልንደረግ መቻላችን ነው።

ይህም ማለት መንግሥት አሊያም አንድ ተቋም በሲም-ካርዴ አማካኝነት እየተከታተለኝ ነው የሚል ስጋት ካለዎት ኢ-ሲም አስጊ ነው።

ለምሳሌ በሆሊውድ ፊልሞች ላይ እንደምንመለከተው የሚዳሰሰውን ሲም ካርድ ከስልክዎ አውጥተው ከጣሉ አድራሻዎን ማግኘት ከባድ ነው።

የኢ-ሲም ካርድ ተጠቃሚ ከሆኑ ግን ስልክዎን ካልጣሉ በቀር ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም።

የቴሌኮምዩኒኬሽን፣ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ተደራሽነት የሚከታተለው ኦሚዲያ የተሰኘው ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ዓመት መጨረሻ 5 በመቶ ስማርት ስልኮች ኢ-ሲም ይኖራቸዋል ይላል።

ይህ ቁጥር በ2024፤ 20 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

አፕል፣ ሁዋዌ እና ሳምሰንግ ስልኮች አንድ ላይ ከግማሽ በላይ የዓለማችን የስማርት ስልክ ገበያን ይይዛሉ። አሁን እነዚህ ስልኮች ኢሲምን ጨምረው መጥተዋል።

ኢ-ሲም፤ ስማርት ስልኮች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የስልክ ኩባንያዎች እያመረቷቸው ያሉ የእጅ ሰዓቶችም ላይ መገጠም ጀምረዋል።

የቴክኖሎጂ ተንታኞች በአፍሪካ የኢ-ሲም ተጠቃሚነት ቀስ በቀስ እያደገ ነው ብለው ያምናሉ። ደቡብ አፍሪካ ሰፊ ተጠቃሚ ያላት አገር ናት።

ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገራት የሞባይል ቴክኖሎጂ እና አገልግሎቶች በ2019 ለአገራቱ ጠቅላላ ምርት የነበራቸው አስተዋጽኦ 9 በመቶ አሊያም 155 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነበር።

ሆኖም በቀጠናው የሚገኙ 800 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እስከ አሁን የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ አይደሉም። ምንጭ ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: