ዮ! ዮ! ጊፋታ

የዎላይታ ዘመን መለወጫ

የዎላይታ ብሔር በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነው፡፡ ከእነዚህ ሀብቶች መካከል የብሔሩ ዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ አንዱ ነው፡፡ ጊፋታ የዎላይታ ሕዝብ በኦሞ ወንዝ ተፋሰስ ቋሚ ኑሮ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲከበር የቆየ፣ ከማንኛውም ባህላዊ እምነትም ሆነ ዘመናዊ ኃይማኖትና የአምልኮ ሥርዓት ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለው የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል ነው፡፡ ጊፋታ ማለት ባይራ(ታላቅ)፣ መጀመሪያ፣ እንደ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል፡፡

ጊፋታ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አእዋፋትና የቤት እንስሳትም ጭምር በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ የዎላይታ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ/ካሌንደር አለው፡፡ በዎላይታ የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡

በበዓሉ “Gifaata Gazzee Abuuna Gaylle” ተብሎ ይዘፈናል፡፡ ይህም የበዓሉን ታላቅነት ለመግለጽ ነው፡፡ አሮጌው ዓመት እየተገባደደ ሲሄድ በንጉሱ(በዎላይታ ንጉስ) አማካሪዎች አማካይነት የዘመን ቆጠራ ባለሙያዎች ወደ ቤተ መንግሥት ይጠሩ ነበር፡፡ ቆጣሪዎቹ ከዚያም ሌሊት ሌሊት እየወጡ የጨረቃን ኡደት መነሻ ለማወቅ የጨረቃን አራት ክፍሎች ማለትም /ፖኡዋ፣ ጡማ፣ ጤሯ፣ ጎባና/ በየትኛው ክፍል እንደሚውል የማወቅ ስራ ይሰራሉ፡፡ በዚህም የዓመቱን የቆጠራ ምልክቶች ይዘው መጥተው የሙሉ ጨረቃዋን ኡደት ተመልክተው ለንጉሱና ለአማካሪዎቹ ያበስራሉ፡፡

የጊፋታ በዓል ቅድመ ዝግጅት፡- የጊፋታ በዓል ከሌሎች በዓላት በተለየ የረዥም ወቅት ዝግጅት ይደረግለታል፡፡ በጊፋታ ሁሉም የቤተሰብ አባላት የየራሳቸው የሥራ ድርሻ አላቸው፡፡ የአባወራዎች ተግባር፡- የጊፋታ በዓል ዝግጅት የሚጀምረው በቁጠባ/”ቆራጱዋ” ነው፡፡

ይኸውም በዕርዱ ዕለት በእርጥብ ቆዳ ላይ የቀጣዩ ዓመት ቁጠባ አንድ ተብሎ ይጀመራል፡፡ ሌላው በጊፋታ ዕለት ወንዶች በሬ ከታረደ በኋላ ከሁሉም የሥጋ ዓይነት፣ ከየዓይነቱ ትንሽ ትንሽ ቆርጠው በባለተራው ቤት ውስጥ በተዘጋጀው ማባያ፣ ማለትም ቆጮ፣ ቂጣ፣ ዳታ በርበሬ ጋር ተቃራጮቹ፣ የ”አሙዋ” አባላት በጋራ ይቋደሳሉ፡፡

ይህም የአንድነትና የፍቅር ማብሰሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሌላው በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከናወን የአካባቢ እድሳት ሥራ ነው። ይህም በወላይታ ብሔር አዲስ ዓመት የመታደስ ምልክት ስለሆነ ሰዎች በግላቸው የቤታቸውን የሳር ክዳን በአዲስ ሳር መቀየር፣ በቤት ውስጥ እና ከውጪ ደግሞ በቤቱ ዙሪያና በአካባቢው የሚገኙ ቆሻሻዎችን በማጽዳት በዓሉን ይቀበላሉ፡፡ እነዚህ ከአባወራ ተግባራት በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የእማወራዎች ተግባር፡- እማዎራዎች ለጊፋታ በዓል ከሚያደርጓቸው ዝግጅቶች የመጀመሪያው ”ኦይሳ ቆራጱዋ” ወይም የቅቤ ዕቁብ ሲሆን ይህም ዋነኛው የእማወራ ተግባር ነው።

በዚህም መሠረት ዓመቱን ሙሉ ለጊፋታ የቆጠቡትን ቅቤ ‘‘በቦቦዳ’’ አጥቢያ ሰብሳቢያዋ ቤት ተሰብስበው የቅቤ ቡና ከጠጡ በኋላ የየድርሻቸውን ተከፋፍለው ይወስዳሉ፡፡ ጊፋታ ካለፈ በኋላም ለቀጣይ ዓመት በየሳምንቱ ቁጠባውን ይቀጥላሉ፡፡ እናቶች በሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ለተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ማለትም ለቆጮ፤ ‘‘ለሙቹዋ’’፤ ‘‘ለባጪራ’’፤ የሚሆኑ የደረሱ እንሰቶችን የመፋቅ ዝግጅቶች ያደርጋሉ፡፡ እንሰት መፋቅ የእናቶች ተግባር ቢሆንም የሚፋቀውን እንሰት መርጦ ማዘጋጀት ግን የአባወራው ድርሻ ነው፡፡

በአባወራው ተለይቶ የተሰጠውን እንሰት ጓደኞቿንና ሴት ልጆቿን በማስተባበር መፋቅና ማዘጋጀት የእማወራዋ ተግባር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የወላይታ ዳታ በርበሬ ያዘጋጃሉ፤ በዓሉ ሲቃረብ ያዘጋጃሉ፡፡ የጊፋታ በዓል ሲቃረብ የሚውሉ ገበያዎች ከእርድ ቀን ቀደም ብሎ የጊፋታ በዓል መቃረቡን የሚያበስሩ በብሔሩ አባላት የሚታወቁ ገበያዎች አሉ፡፡ እነሱም “ሃሬ ሀይቆ”፤ ”ቦቦዶ” እና “ጎሻ” በመባል የሚታወቁ ሲሆን ሌላው ደግሞ “ ቃኤ ጊያ “ ይባላል፡፡

1. ሃሬ ሀይቆ ”Hare hayiqo”፡- ቀጥተኛ ትርጉሙ የአህያ መሞቻ እንደ ማለት ሲሆን ይህም በወቅቱ አህዮች ያለባቸውን ድካም ለማሳየት ነው፡፡ በዓሉ እየተቃረበ በመጣ ቁጥር ሁሉም ሰው ለበዓሉ ዝግጅት እህልና ሌሎችን ቁሳቁሶች በአህዮች እየጫነ ወደ ገበያ ያወጣል፡፡ ይህንን ጊዜ ከሌላዉ የሚለየዉ አንድ አህያ በቀን ከሦስት ጊዜ በላይ እየጫነ ወደ ገበያ መመላለሱ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህ ወቅት በሕብረተሰቡ የጊፋታ በዓል ዝግጅት ሸመታና ሽያጭ የሚጀመርበት ነው፡፡

በመሆኑም ከሌሎች ገበያዎች በጣም የተረጋጋ እንቅስቃሴ የሚታይበት ገበያ ነው፡፡ 2. ቦቦዳ “Bobooda”፡- ሁለተኛው በሃሬ ሀይቆ ሳምንት የሚውለው ገበያ ሲሆን ይህ ገበያ ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በአዳዲስ ነገሮች የተሞላ ገበያ ነው፡፡ በዚህ ገበያ ገበያተኛው ቀድሞ ወደ ገበያ የሚመጣበትና በአብዛኛው ሴቶች የሚበዙበት ነው፡፡ ሴቶች ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች የሚሸምቱበት ሆኖ በዚህ ገበያ የሸክላ ዕቃዎች ሽያጭና ግዥ በእጅጉ ይደራል፡፡ ከዚህም ሌላ በዓሉ እየተቃረበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ሰዎች ባር ባር(ፍርሃት ፍርሃት) ይላቸዋል፡፡

የፍርሃቱ ምንጭም ከበዓሉ ትልቅነትና ስፋት አንጻር ምን ይጎልብኝ ይሆን በማለት ቤተሰቡ በሙሉ በፍርሃትና በጭንቀት የሚዋጥበት ወቅት ስለሆነ ነው፡፡ 3. ጎሻ “Gooshsha”፡- ሶስተኛው ሳምንት ገበያ ጎሻ የሚባል ሲሆን ጥሬ ትርጉሙ እብደት እንደ ማለት ነው፡፡ ሰዎች ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ከንጋቱ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ ወደ ገበያ ይሰበሰባሉ፡፡

በገበያ ውስጥ እርስ በርስ የሚገፋፉበት፣ የሚገጫጩበት፣ እንደ እብድ የሚይዙትን የሚጨባጡትን የሚያጡበት ፣ ነገር ግን የማይቀያየሙበት የገበያ ውሎ ነው፡፡ ቃኤ ጊያ፡- ሌላውና የመጨረሻው ፣ ማሳረጊያው ፣ ‘‘ቃኤ ጊያ የሚባለው ሲሆን ይህም በእርዱ ቀን፣ እሁድ ዕለት ማለትም ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ ከሌሊቱ 10፡00 እስከ ጧቱ 2፡00 ሰዓት የሚቆም ገበያ ነው፡፡

በዚህም ለበዓሉ የሚያስፈልግ ሆኖ ድንገት የተረሳ ነገር ካለ ይሸመታል፡፡ ለእርድ እሁድ 15 ቀናት ሲቀሩት ጀምሮ ፣ በበዓሉ ወቅትና ከበዓሉ በኋላ በሚኖሩት የመዝናኛ ሳምንታት ምንም ዓይነት ሥራ ስለማይሠራ ለከብቶች የሚበቃ ሳር በወንድ ልጆች ይታጨዳል፡፡

በአሞሌ ጨው የሳር ድርቆሽ ይዘጋጃል፡፡

ከዚህም ሌላ እንጨት በአባቶችና በታላላቅ ወንድ ልጆች ይፈለጣል፤ የቆጮ ቆረጣ በእናቶችና በሴት ልጆቻችው ይደረጋል፤ በድሮ ጊዜ ማሽላና በቆሎ በባህላዊ ወፍጮ ተፈጭቶ ዱቄቱ ይዘጋጃል፤ ዳታ በርበሬ የመለንቀጥ ሥራ በሴቶች ይሠራል፡፡ የጎሻ ሳምንት እየተገባደደ ሲመጣ የሚውለው ሀሙስ “ኮሰታ ሃሙሳ”(ሻጋ ጋላሳ) ይባላል፡፡ ትርጉሙ የእንኩሮ ሃሙስ ማለት ሲሆን ዓርብ ሱልኣ አርባ(ብዛ ጋላሳ) ይባላል፡፡

ይህም በየቤቱ ለቦርዴ የሚሆን እህል የሚዘጋጅበት ሲሆን ለሆድ ማሟሻ ጎዳሬ “Boynaa Cadhdhiyaa” እና ከቦዬ የሚዘጋጅ “Boyinaa Pichaata” የሚበላበት ዕለት ነው፡፡ ቅዳሜ ፣ የባጪራ ቅዳሜ “Baaccira qeeraa” የሚባል ሲሆን በዚሁ ዕለት ለእሁድ(የእርድ) ዕለት ሆድ ማለስለሻ ምግቦች ይበላሉ፡፡ የበዓሉ አከባበር፡- የዕርድ ዕለት ጧት ወፍ እንደተንጫጫ በቤተ መንግሥት 12 ጊዜ ነጋሪት ይጎሰማል፡፡

በዚህን ጊዜ ከሁሉም የወላይታ አካባቢዎች የ ‘‘አላና’’ ኃላፊዎች ይሰበሰባሉ፡፡ የነጋሪቱን ድምጽ እንደሰሙ በሬ አራጆች ሥራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የአላና ኃላፊዎች ወደ ግብር አዳራሽ ይገባሉ፡ቀጥሎም የወላይታ ባህላዊ ንጉስ በክብር ወደ አዳራሹ ከገቡ በኋላ ለሰማይ አምላክ ምስጋና ይቀርባል፡፡ ለበዓሉ የተዘጋጀውን ቦርዴ ንጉሱ ከቀመሱ በኋላ እርስ በርስ፣ የፍቅር መግለጫ በሆነው የ”ዳጌታ“ ሥርዓት ቦርዴውን ይጠጣሉ፡፡ ለበዓሉ የታረደው ሥጋ በዳታ በርበሬ፣ በቂጣና በጎዴታ ቆጮ ይቀርባል፡፡ ሁሉም በልተውና ጠጥተው ወደየአካባቢያቸው ይመለሳሉ፡፡

ይህም በብሔሩ የጊፋታ “ቃይዴታ” ሥርዓት የሚባል ሲሆን የተጣላ የሚታረቅበት፣ ሰዎች ፍቅራቸውን ከአንድ ማዕድ በመቁረስ የሚያድሱበት ፣ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ ነው፡፡ በዕለቱ የበሬ ሥጋ በጋራ የሚያርዱ የ”አሙዋ” አባላት በየቤታቸው ጠዋት ሙቹዋ ወይም ባጭራ በቅቤ ቡና ይቀምሱና ቢላዋና ቅርጫት አስይዘው ወንድ ልጆቻቸውን ወንድ ልጅ ከሌላቸው ሴት ልጆቻቸውንይዘው በሬ ወደሚታረድበት ደጃፍ ይሄዳሉ፡፡

የበሬውን ቆዳ ከገፈፉ በኋላ መጀመሪያ ፊኛው ወጥቶ ለልጆች ይሰጣል፡፡ ልጆች ሥጋው ታርዶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ፊኛ በእግራቸው እየመቱ ይጫወታሉ፡፡ በሬ በሚታረድበት ቤት ደጃፍ የተሰበሰቡ ሰዎች “ባጭራ” ወይም “ሙቹዋ” ይበላሉ- ከቅቤ ቡና ጋር ፡፡ ባህላዊ መጠጥም ይቀርባል፤ እነዚህ ሰዎች በሬውን በጋራ ያርዳሉ፤ በሬው እየታረደ እያለ ከሁሉም የሥጋው ብልት ይቆረጥና የ”አሙዋ”አባላት የፍቅር መግለጫ ነው ተብሎ ስለሚታመን በጋራ ይቋደሳሉ፡፡

በመቀጠልም ዕጣ ጥለው ሥጋውን ከተከፋፈሉ በኋላ ለሚቀጥለው ዓመት ጊፋታ በዓል በሬ መግዣ ተቀማጭ በታረደው በሬ ቆዳ ላይ መጣል ይጀምራሉ፡፡ ይህ የቁጠባ ሥርዓት ከ”ጎሉዋ ኢጌታ” በኋላ በየሳምንቱ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ የአመጋገብ ሥርዓት፡ የግፋታ ዕለት ከንጋት ጀምሮ ቤት ውስጥ የተለያዩ ዝግጅቶች ይደረጋሉ፡፡ እናቶች ከተዘጋጀው ዳታ ለዕለቱ የሚበቃውን ከፍለው ቅቤ በመጨመር በእሳት ያንተከትካሉ፣ ቂጣ፣ ቆጮ ያዘጋጃሉ፡፡

ከዚህም ሌላ “ኤርጊያ” የሚባለው ያልተበሳሳ ኮባ ቅጠል ተቆርጦ ሳሎን ውስጥ መሬት ላይ እንዲዘረጋ ይደረጋል፡ ፡ አባት ካመጣው ሥጋ መካካል በጥሬ የሚበላውን በማዘጋጀት በቢላዋ እየቆረጠ በኮባው ቅጠል ላይ ዙሪያውን ያስቀምጣል፡፡ ቆጮና ቂጣም በተመሳሳይ ሁኔታ ይደረጋል፤ በመሃል በመሃሉ ዳታ በርበሬ በወጪት ተደርጎ ይቀመጣል፡፡ ማዕዱ ከቀረበ በኋላ ከዓመት ዓመት በሰላም ያሸጋገረው አምላክ እንደየአምልኮ ስርዓቱ ይመሰገናል፡፡

አባት ከሁሉም በፊት ከተዘጋጀው ማዕድ እናትን ያጎርሳል፡፡ በመቀጠልም በማዕዱ ዙሪያ የተቀመጡትን ልጆች ሁሉ ያጎርሳቸዋል። ቀጥሎም የቤተሰቡ አባላት የየራሳቸውን መመገብ ይጀምራሉ፡፡ የጉሊያ አቀጣጠል ሥርዓት ፡- ጉሊያ የወላይታ ብሔር የጊፋታ በዓልን በእሳት ብርሃን የሚያከብርበት ሥርዓት ሲሆን የሰኔ “ኩሻ” ወር ማብቂያ ሦስት ቀናት ሲቀሩት የሠፈር ወጣቶች ብዙ አገልግሎት የማይሰጡ እንጨቶችን ከጫካ ውስጥ ቆርጠው እየጎተቱ አንድ ቦታ ይከምራሉ፡፡ የተከመረው እንጨት ለጊፋታ በዓል ሁለት ሳምንት ሲቀረው እንዲቆም ይደረጋል፡፡

የተከመረው እንጨት የጊፋታ ወር መጀመሪያ ጨረቃ በታየች አራት ቀናት መካከል በሚውለው እሁድ (ሹሃ ወጋ) እርድ ተከናውኖ ሥጋ በተበላበት ማታ የሚከበር ታላቅ ሥነ-ሥርዓት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ማታ አንድ ሰዓት አካባቢ የሠፈር ወጣት ወንዶችና አባቶች ከየቤታቸው ቺቦ(ጢፋ) በመያዝ በጉሊያው ዙሪያ ይሰበሰባሉ:: በአካባቢው ታዋቂና ታላቅ የሆነ ሰው ጉሊያውን በእሳት እንዲለኩስ ይጋበዛል፡፡

የእርድ ዕሁድ ማግስት ሰኞ ታማ ሰይኖ ይባላል፡፡ ጥሬ ትርጉሙ የእሳት ሰኞ ማለት ነው፡፡ ይህም እሁድ ዕለት በሁሉም ሰው ቤት እስከ ሌሊት ድረስ እሳት ስለሚነድ በነጋታው ሰኞ ማንም ሰው ወደ ጎረቤቱ እሳት ለመጫር አይሄድም፡፡ ከግፋታ ቀጥሎ የሚመጣው ሁለተኛው ቀን ማክሰኞ “ጪሻ ማስቃይኖ” ይባላል፡ ፡ ይህም የመልካም ምኞት አበባ ስጦታዎች የሚለዋወጡበት ቀን ነው፡፡

በዚሁ ዕለት የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ “ኮርማ ጪሻ” ተብሎ የሚጠራው ነጭ አበባ ፣ እሱም ካልተገኘ ደግሞ አደይ አበባ የተባለው የአበባ ዓይነት ተይዞ እንኳን አደረሳችሁ! ጊፋታ ዮዮ! እየተባለ አማች፣ አበልጅ ቤት እንዲሁም ደግሞ እንደየቅርበቱ ዘመድ አዝማድ ቤት እየተኬደ መልካም ምኞት ይገለፃል፡፡ የአበባ ስጦታው ለቤቱ አባወራ የሚሰጥ ሲሆን ፣ አባወራው በቀኝ እጁ አበባውን ይቀበልና ከምሶሶ ጋር ያስራል፡፡

እነዚህ ሁለት ዓይነት አበቦች በጊፋታ ወቅት ብቻ የሚፈኩ አበቦች ስለሆኑ አባወራው አበባዉን ከተቀበለ በኋላ ጊፋታ እናንተን አይቁጠር ፣ እናንተ ጊፋታን ቁጠሩ፣ “Gifaatay Inttena Qoodoppo Initte Gifaataa Qoodite” ከዓመት ዓመት በሰላም ያድርሳችሁ በማለት ይመርቃሉ፡፡ ስጦታ አምጪዎቹ የሚበላና የሚጠጣ ነገር ተጋብዘው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ በነጋታው ‘‘ጋዜ ኦሩዋ /Gazze Oruwaa” ሲሆን ይህም ሰዎች አጠቃላይ ሀሳባቸውን ወደ መዝናኛ የሚያደርጉበት ሆኖ ታላቁ የጊፋታ ጨዋታ ጋዚያ” Gazziyaa”መድመቅ የሚጀምርበት ዕለት ነዉ፡፡

በዚህ በተከታታይ ለሁለት ሳምንታት በሚቆየዉ ጨዋታ የመንደሩ ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች በአካባቢው ታዋቂ ሽማግሌ ደጃፍ ተሰብስበው ወንዶች ‘‘ሃያያ ሌኬ ’’ እያሉ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው ሎሚ ከልጃገረዶች በመለመን ለትዳር የሚፈልጓትን የሚመርጡበትና የሚያባብሉበት፣ ሴቶችም እንደ አስፈላጊነቱ ምላሽ እየሰጡ የሚጫወቱት የጨዋታ ዓይነት ነው፡፡ ‘‘ከጋዜ ኦሩዋ’’ ጀምሮ ተቆጥሮ የሚመጣው ሶስተኛ ረቡዕ ‘‘ጎሏ ኦሩዋ /Gooluwaa Oru wa” ይባላል፡፡

ይህም ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ የቆየው የበዓል ዝግጅትና አጠቃላይ የጊፋታ በዓል ሥነ-ሥርዓት አብቅቶ የሚሸኝበት ቀን ሲሆን ከበዓሉ ጋር ተያይዞ በነበረው የመዝናኛ ወቅት ምክንያት በሰዎች ዘንድ ስንፍና እንዳይገባ በማለት ሁሉም ችቦ እያቀጣጠሉ ለሚመጣው በዓል አምላክ በሰላም እንዲያደርሰው በመመኘት ጊፋታን ይሸኛሉ፡፡ ይህም የመዝናኛ የዕረፍት ወቅት አብቅቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ወቅት በመሆኑ “Oruwaappe Hepinttay Ofintta” ይባላል፡፡ ከዕሮብ በኋላ ዕረፍትና መዝናናት የሉም፤ ሥራ ተጀምሯልና ወደ ሥራ እንግባ እንደማለት ነው፡፡

ይህንን በዓል ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጋር አብረው ለማክበር ጥሪ ያቀረቡት የዎላይታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ሀብቴ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ከፌዴራል ባህልና ስፖርት: ቅርስ ጥናትና ጥበቃ፡ ከደቡብ ክልል መንግስት እና ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከዎላይታ ዞን አስተዳደር ጋር በመሆን ብዙ ጥረት የተደረገበት ነው ብለዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም የዘንድሮ ጊፋታ በዓል የሚከበረው መስከረም 14 የቋንቋና ባህል ስምፖዚየምና በሩጫ ውድድር፣ በመስከረም 15 ዋናው የጊፋታ በዓል በደማቅ ይከበራሉ፡፡ ለበዓሉ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የአካባቢው ተወላጆች ኑ በዓሉን በአንድ ላይ እናክብር ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል ስል የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘገባ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *