በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው ያለአግባብ ደመወዝ ሲከፈላቸው የነበሩ 346 ሠራተኞች ከሥራና ከደመወዝ መታገዳቸውን የካፋ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

ሰሞኑን የዞኑ አስተዳደር የወረዳና ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤቶችን አፈጻጸም ገምግሟል፡፡

በመሆኑም ለበርካታ ጊዜያት ከሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጋር ተያይዞ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለማጥራት እንዲቻል በባለፈው በጀት ዓመት ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንደሻዉ ከበደ ገልጸዋል።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለማጣራት በተደረገው እንቅስቃሴ የተወሰኑ ወረዳዎች  በትጋት መስራታቸውን የገለጹት አቶ እንዳሻው አልፎ አልፎ ክፍተትና ጉድለት የታየባቸው ወረዳዎች ፈጥነው ወደ ተግባር እንዲገቡ አሳስበዋል።

በዚህ መሠረት ከቀረቡት 2 ሺ 928 የትምህርት ማስረጃዎች መካከል 3መቶ 46ቱ ሐሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል ያሉት ደግሞ በዞኑ አስተዳደር ጽ/ቤት የመልካም አስተዳደርና አካባቢ ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ታሪኩ ወልደ ሚካኤል ናቸው ፡፡

በማጣራት ሂደቱም አስተዳደራዊ እርምጃ ከተወሰደባቸው ግለሰቦች መካከል 34ቱ በተለያዩ የአመራር ቦታ ላይ ሲሰሩ የነበሩት መሆናቸውን የገለጹት አቶ ታሪኩ በቀሪዎች ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንዲቻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በመሆኑም 18 ሚሊየን ብር ከብክነት መታደግ መቻሉን ገልጸው የተሻለ አፈፃፀም ያከናወኑት ቢጣ፣ ሺሾ እንዴና ጨና ወረዳዎች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ተገቢ የማጣራት ሥራ ማከናወን ያለባቸው ደግሞ የዞን ማዕከል፣ ግምቦ፣ ጌሻ፣ ዴቻ ወረዳዎችና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር መለየታቸውን አቶ ታሪኩ ገልጸዋል፡፡ 

በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ  ምክንያት ለቦታው የሚመጥን የሰው ሀይል ዕድል ተነፍጎና ያለዕውቀት በደል በተገልጋይ ሲፈጸም መቆየቱን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ ለበርካታ ጊዜያት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ሲነሳ መቆየቱን ገልጸዋል።

የማጣራቱን ሂደት የተዋቀረው ግብረ ሃይል አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው አስፈላጊውን ድጋፍ በማበርከት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል ስል ደረቴድ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *