1667750536537

የኢትዮጵያ መከላከያና የህወሃት ወታደራዊ አመራሮች ሰኞ ጥቅምት 28፣ 2015 ዓ.ም በናይሮቢ እንደሚነጋገሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን ገልጸዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ይህንን የተናገሩት በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለውጭ ዲፕሎማቶችና ለአለም አቀፉ ማህበረሰቡ ገለጻ ባደረጉበት ወቅት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ጥቅምት 26፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ከስምምነቶቹ መካከል አንዳንዶቹ በአስቸኳይ መተግበር የሚጠበቅባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል በወታደራዊ አመራሮች መካከል የንግግር መድረክ ማመቻቸት አንዱ ነው ብለዋል።

የሁለቱወገኖች ወታደራዊ አመራሮች ከወዲሁ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን መግለፃቸውን የጠቆመው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ወታደራዊ አመራሮቹ በቀጣይ ስለሚከናወኑ ሂደቶች የፊታችን ሰኞ በአካል ተገናኝተው እንደሚወያዩም በኃገርውስጥ መገናኛ ብዙኃን በተላለፈው ንግግራቸው ጠቅሰዋል።

የፌደራሉ መከላከያና የህወሃት ወታደራዊ አመራሮች በአካል ተገናኝተው ስለ ትጥቅ መፍታት እንደሚነገጋሩ የተናገሩት አማካሪው “ትጥቅ ለሚፈቱት የህወሃት ታጣቂዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚለው” ሌላ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሬድዋን “የህወሃት ታጣቂዎች ትጥቅ ከፈቱ በኋላም” የትግራይ ክልል እንደ ሌሎች ክልሎች በቂ የሚባል ልዩ ኃይል እንደሚደራጅለትም አስረድተዋል።
“ህወሃትን ትጥቅ ማስፈታት ብለን የጸጥታ ኃይል በክልሉ  እንደሚደራጅ ስንናገር አንዳንድ አጋሮች በዚህ ግርታ ሊገባቸው ይችላል። ክልሎች የራሳቸው የጸጥታ ኃይሎች አላቸው። የትግራይ ክልል የራሱ የጸጥታ ኃይል እንዲኖረው ያለውን መብት አንክድም” ብለዋል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ የትግራይ ክልል ፖሊስና “የተመጠነ የጸጥታ ኃይል አደረጃጀት እንደሚኖሩት” ጠቅሰው “የሚደራጀው ኃይል ተጠሪነቱ ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት እንጂ የአንድ ፓርቲ አይሆንም” ብለዋል።