ዲሽታግና በሚለው ነጠላ ዜማው ተወዳጅነትን ያተረፈው ታሪኩ ጋንካሲ በተገኘባቸው መድረኮች ስለ ሠላም እና ፍቅር በመስበክ ይታወቃል።

ከአድናቂዎቹ ጋር ያስተዋወቀው የመጀመሪያ ሥራውና በአሪ ብሔረሰብ አዲስ ዓመት የተሰየመው ‘ዲሽታግና’ም የሚያወሳው ስለፍቅር እና ሠላም ነው።

በብሔረሰቡ ይህ የዘመን መለወጫ በዓል አብረው የሚበሉበት፣ የሚጠጡበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ለሌላቸው የሚያካፍሉበት እና የሚደጋገፉበት በዓል ነው።

ታሪኩ ሙዚቃውን ከለቀቀ በኋላ ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ ምልልስ ሙዚቃውን ለመሥራት የተነሳው ይህ ፍቅር አዘልና አስታራቂ ባህል ስለገዛው መሆኑ ተናግሯል።

ዲሽታግና ከተለቀቀ አንድ ዓመት ቢሆንም እስካሁን 29 ሚሊዮን ሰዎች በዩቲዩብ ተመልክተውታል።

ትውልደ ሴኔጋላዊው እና በዜግነት አሜሪካዊ የሆነው ድምጻዊ ኤኮን ሙዚቃውን ሪሚክስ አድርጎታል።

ኤኮን ሪሚክስ ለማድረግ የፈለገበትን ምክንያት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ሲናገር “ . . . ዲሽታግና በአሁን ሰዓት በጣም ከወደድኳቸው ሥራዎች መካከል አንዱ ነው. . .” ብሎ ነበር።

በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት የውትድርና ሕይወትን ተቀላቅሎ እንደነበር የሚናገረው ታሪኩ፣ ብዙውን ጊዜ ስለጦርነት አስከፊነት ይናገራል።

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎም ከአንድ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ “ለቅስቀሳ” በተዘጋጀውና የሙዚቃ ሥራውን ለማቅረብ በተጋበዘበት ሰፊ መድረክ ላይ “ጦርነት ይብቃ!” ሲል ስለ ሠላም መናገሩ ይታወሳል።

ይህም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ እና ዝግጅቱ ከተሰናዳበት አላማ ጋር የሚቃረን ነው በሚል ከተለያዩ ወገኖች ከባድ ትችት እና ተቃውሞ አስከትሎበታል።

በዚህም ሳቢያ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መድረኮች ላይ ቀርቦም እያለቀሰ ይቅርታ መጠየቁ ይታወሳል።

“በእርግጥ ‘ጦርነት ይብቃ!’ ማለት፣ስለ ሠላም መስበክ ይቅርታ ያስጠይቃል ወይ?” ሲሉ ከእርሱ ጎን የቆሙም በርካቶች ነበሩ።

ይህን በተናገረ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ታዲያ የፌደራሉ መንግሥት እና የህወሓት አመራሮች በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ለአስር ቀናት የዘለቀ ንግግር ካደረጉ በኋላ ግጭት ለማቆም ተስማምተዋል።

ይህንንም ተከትሎ ታሪኩን ስለ ሠላም ስምምነቱ ምን ተሰማህ? አልነው።

ታሪኩ ጦርነቱን ለማስቆም በተደረሰው የሠላም ስምምነት “የተሰማው ደስታው ወደር እንደሌለው” ገልጿል።

“የሰው ልጅ ቢኖረውም፣ ባይኖረውም፣ ቢደላውም፣ ቢከፋውም ሠላም ሲኖር ነው ደስ የሚለው” የሚለው ታሪኩ፣ “ያኔ በንግግሬ ስወገዝ እንዳለቀስኩት ሁሉ፣ መስማማታቸውን ስሰማ የዚያ ትውስታ አስለቅሶኛል” ብሏል።

በተዘጋጀው የቅስቀሳ መድረክ ላይ ምን ነበር ያለው?

በተዘጋጀው መድረክ ላይ የሙዚቃ ሥራውን ለማቅረብ በመንግሥት ተጋብዞ እንደነበር የሚናገረው ታሪኩ፣ በመድረኩ ላይ ስለሠላም እና እርቅ ለመናገር ቀድሞ አስቦበት ወደ መድረኩ እንደወጣ ያስታውሳል።

ከዚያም “አፈ ሙዝ አያስተምረንም፣ ጦርነት አያስተምረንም፣ ችግር አያስተምረንም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉም ጀግና ነው፤ ማንም ፈሪ የለም፤ ማንም ጀግና የለም። ሁላችንም አንድ ስለሆንን እባካችሁ ሠላም ያስፈልገናል” የሚል ንግግር እንዳደረገ ይናገራል።

ታሪኩ፣ ይህንን ያልኩት የጦርነት እና የጥል መጨረሻው እርቅ እንደሆነ ስለማውቅ፣ ሰው የበለጠ ሳይጎዳ በጊዜ ጦርነት እንዲቆም ስለፈለኩ እንዲሁም “ከሞትኩም እውነት ተናግሬ ልሙት፣ ታሪክ ነው” ብዬ ነበር ይላል።

“ለልማት አባይን እንደደፈርነው ሁሉ እኔም ለሠላም ደፍሬያለሁ” ሲልም ያክላል።

አንዳንድ ሰዎች “ቦታውን ያላገናዘበ ንግግር ነው” ሲሉ ትችት ሰንዝረውበታል።

ታሪኩ ግን “የፈጣሪን ቃል ለመናገር ቦታ መምረጥ አያስፈልግም። ስለ ሠላምና ፍቅር ነው ያወራሁት” ሲል ይሞግታል።

ታሪኩ ይህን ያለው ከሁለት ዓመት በፊት የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀሙትን ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልል ተስፋፍቶ፣ ውጊያው በተጋጋለበት እና “የህልውና ዘመቻ” ቅስቀሳ በሚካሄድበት ወቅት ነበር።

ይህንን ከተናገረ በኋላ ከመንግሥት አካላት የደረሰበት በደል ባይኖርም፣ በአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና ግለሰቦች ውግዘት እና ማስፈራሪያዎች እንደደረሰበት ይናገራል።

በኢቢኤስ ቴሌቪዢን ላይ ቀርቦም ሲያለቅስና የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሲጠይቅ ታይቷል።

ታሪኩን ያስለቀሰው ምን ነበር?

ታሪኩ “በወቅቱ ያስለቀሰኝ ሰዎች ስላልተረዱኝ ነበር” ይላል።

“እዚች ምድር ላይ ያለ ሰው እውነት የጠፋበት መሆኑ፣ እያወቅን ወደ ገደል ስንገባ ሠላምን ጠልቶ እንገዳደል እንሙት ሲሉኝ፣ እውነት ተደብቆ እኔ በውሸት ስፈረጅ እሱ ነው ያስለቀሰኝ” ሲል በወቅቱ ያስለቀሰውን ምክንያት ተናግሯል።

ታዲያ ይህ ይቅርታ ያስጠይቃል ወይ ያልነው ታሪኩ፣ ይቅርታውን የጠየቀው በንግግሩ ተጸጽቶ ሳይሆን “የበደሉ ብቻ ሳይሆን የተበደሉም ይቅር እንደሚሉት ነው” ሲል ይህንንም ፍቅርን ለማሳየት ያደረገው እንደሆነ ገልጿል።

“እየሱስም መስቀል ላይ ተሰቅሎ ይቅር ይበላቸው ነው ያለው፤ እሱ ያስተማረን ይህንን ነው። እኔም ለአገሬ ከፍ ዝቅ ተደርጌ ተሰድቤያለሁ። ግን ይህ ታሪክ ነው” ብሏል።

በደረሰበት ውግዘትና ወቀሳ ወደ ትውልድ አካባቢው ለመሄድ መገደዱን የሚናገረው ታሪኩ፣ በሄደበትም ከአንዳንድ ሰዎች ተመሳሳይ ትችቶችን እንዳስተናገደም የቅርብ ጊዜ ትውስታው ነው።

ታሪኩ በቅርቡ “ሬይዳዬ” የተሰኘ ነጠላ ዜማ ለአድማጭ ጆሮ አድርሷል። በዚህም ሙዚቃው ሠላም እንዲወርድ ፈጣሪውን ተማጽኖበታል።

ታሪኩ ከደረሰበት ውግዘትና ወቀሳ በኋላም ስለ ሠላም እና ፍቅር ያለው አቋም አለመቀየሩን ይናገራል።

“አውቀን፣ ሳይገባንም፣ ገብቶንም የበተናቸውን፣ ያስራብናቸውን፤ አሁን ደግሞ አንድ ሆነን ትናንት ለጦርነት ያዋጣው ሁሉ አሁን ደግሞ ለሠላም ያለንን አዋጥተን የተሰቃየውን ሕዝብ እንደ ጉዳቱ መጠን መርዳት አለብን። አባቱ ለሞተበት አባት፣ ወንድሙን ላጣው ወንድም፣ እህት ላጣ እህት መሆን አለብን። መንግሥትም ሕዝቡን ከገባበት ሐዘን መመለስ አለበት” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።

ከስምምነቱ በኋላ ያለው ተስፋ

ከስምምነቱ በኋላ ኢትዮጵያ ሠላም ሆና አያለሁ የሚል ተስፋን ሰንቋል።

ሰዎች ያለ ደኅንነት ስጋትና ጭንቀት ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ በሠላም ሲንቀሳቀሱ፣ ሲገበያዩ፣ ሲረዳዱ፣ ሲጠያየቁ ማየትም ምኞቱ ነው።

የተፈጠረው ፖለቲካው አለመግባባት ለበርካታ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ዳርጎናል ሲልም ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በመዋደድ፣ ለሰላም መቆም፣ ያለው ለሌለው በማካፈል ሠላም እንዲያመጡ ይማጸናል።

“ሰው ማጥፊያ የጦር መሣሪያ የሚገዛበት ገንዘብ፣ ሰው የሚደሰትበት ነገር እንዲሰራበት፣ አንዱ አንዱን ለመገደል የገዛነውን መሣሪያ ጥለን አንድ የሚያደርገንን፣ ረሃባችንን የሚያጠፋልንን መሣሪያ መግዛት አለብን። ይህም በፍቅር ይሆናል” ብሏል።   ምንጭ ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

%d bloggers like this: