የዎላይታ ልማት ማህበር የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ባለበት አከባቢ ያስገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ፡፡
የዎላይታ ልማት ማህበር በተቀናጀ ጤና የትኩረት አቅጣጫ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እንደሚያከናውን ይታወቃል፡፡ ማህበሩ ከምስረታው ጀምሮ በተለይም ከአካል ጉዳተኝነት ጋር በተያያዘ በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎች በርካታ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፤ በኤች.አይ. ቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር፤ የጤና መረጃዎችን በማዳረስና ለህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የራሱን ድርሻ እያበረከተ ይገኛል፡፡
ከሰሞኑ ልማት ማህበሩ አሜሪካን ሀገር ከሚገኝ ሴንትራል ሃይላንድስ ፋውንዴሽን (Central Highlands Foundation) ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በባይራ ኮይሻ ወረዳ ወይዴ ማሳና ቀበሌ የንጹህ መጠጥ ውሃ በመገንባት አጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል፡፡ ከ205 ሺህ ብር በላይ የፈጀው ይህ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ስራ ምንጩን ከቦታው ማጎልበት፣ አንድ ኪሎ ሜትር የቧንቧ ዘርጋታ እና አንድ የውሃ ማደያ (ቦኖ) ግንባታ ያካተተ መሆኑንና ከዚህ በፊት የአካባቢው ህብረተሰብ የነበረበትን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የሚቀርፍ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዎላይታ ልማት ማህበር ከዚህ ቀደም ከሴንትራል ሃይላንድስ ፋውንዴሽን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በኪንዶ ዲዳዬና ዳሞት ሶሬ ወረዳዎች በሶስት ቀበሌያት ምንጮችን በማጎልበት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዳደረገና በካዎ ኮይሻ ወረዳ ላሾ ከተማ 50 ሺህ ሊትር ውሃ የሚይዝ ማጠራቀሚያ ግንብቶ ማጠናቀቁን በዜናዎቻችን ማስነበባችን ይታወሳል ሲል ልማት ማህበሩ አስተውቋል።
