

የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት የደረሱትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በትግራይ በምግብ ፍጆታዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ መረጋጋት ታየ።
የቢቢሲ ጋዜጠኛ ከመቀለ እንደዘገበው የጤፍ ዋጋን ጨምሮ የእህልና ሌሎች ዋጋ ንረቶች አሁን ድንገተኛ መረጋጋትን አሳይተዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመቀለ ነዋሪዎች ስምምነቱ እንዳስደሰታቸውና በበጎ እንደተመለከቱት ተናግረዋል።
ብዙዎች ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ፍላጎታቸው መሆኑም ተናግረዋል።
ዘጋቢያችን እንደታዘበው ያነጋገራቸው በርካታ ሰዎች መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።
የሰላም ስምምነቱ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የእህልና ጥርጥሬ ገበያ መረጋጋት አሳይቷል። በተለይ መረጋጋቱ በመሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች ላይ በይበልጥ ተስተውሏል።
የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ 14ሺህ ብር የነበረ ሲሆን የሰላም ስምምነቱን ዜና ተከትሎ ወደ 8ሺህ ብር ዝቅ ብሏል።
ስንዴም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ9ሺህ ወደ 3ሺህ ወርዷል።
በተመሳሳይ የዘይት፣ የስኳር እና የበርበሬ ዋጋም መጠነኛ መረጋጋትን አሳይቷል።
የቢቢሲ ዘጋቢ በስፍራው ተዘዋውሮ እንደታዘበው ከሆነ የበርካታ ሰዎች ዋናው መነጋገሪያ በፕሪቶሪያ ባለፈው ሳምንት የተፈረመው የሰላም ስምምነት ነው።
ወ/ሮ ራሔል አባይ የተባሉ የሁለት ልጆች እናት በሰላም ስምምነቱ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጠዋል።
“…ጦርነቱ በሚደረግበት ቦታ የምንኖረው እኛ ነን። መሬት ላይ ምን እንዳለ የምናውቀው እኛ ነን። አሁን ቢያንስ የድሮን ጥቃት ሳያሳስበን መንቀሳቀስ ጀምረናል።” ብለዋል ወ/ሮ ራሔል።
እንደዘጋቢያችን ከሆነ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደ ወ/ሮ ራሔል ያለ አመለካከት ነው ያላቸው።
የ32 ዓመቱ በላይ ታከለ የመቀለ ነዋሪ ሲሆን በሰላም ስምምነቱ ዙርያ ተጠይቆ ሲመልስ “እኛ የትግራይ ሕዝቦች እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ በሰላም መኖርን ነው የምንሻው። ጦርነቱ ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን እኛ ነን የምናውቀው። አሁን የምንሻው ፈራሚዎቹ ወገኖች ስምምነቱን እንዲያከብሩ ነው።” ብሏል።
የቢቢሲ ዘጋቢ ያነጋገራቸው በትግራይ የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ አማራና ሌሎች ከተሞች የሚወስዱ መንገዶች ሁሉ እንዲከፈቱና የሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ ይሻሉ።
ብዙ ነዋሪዎችን እያነጋገረ ያለው የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት ጉዳይ ሲሆን በርካታ ሰዎች ሕገ መንግሥቱ መከበር እንዳለበት ቢያምኑም በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሙሉ እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። ይህም የሆነው ባለፉት ሁለት ዓመታት መከላከያ በርካታ ሰብአዊ ጥሰቶችን በመፈጸሙ ነው ይላሉ።
ተስፋዬ አድሃኖም በአዲ ሐቂ መቀለ ነጋዴ ሲሆን ወራሪው የኤርትራ ኃይል መቼ ነው ከአገራችን የሚወጣው ሲል ጠይቋል። ጨምሮም፣ ‘የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለምን በኤርትራ ጉዳይ ዳተኛ እንደሆነ አይገባኝም’ ይላል።
ይህ በእንዲህ የትግራይ ዳያስፖራ አባላት በሰላም ስምምነቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞና ጥርጣሬ ከመግለጽ አልተቆጠቡም። በተለይም የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ የሚዋጥላቸው አልሆነም።
በተለይም በስምምነቱ ውስጥ የኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ መውጣት እንዳለበት በማያሻማ ሁኔታ መገለጽ ነበረበት የሚል ቅሬታን ያሰማሉ።
ቢቢሲ ተዘዋውሮ እንደተመለከተው የመቀለ ሰማይ አሁን ሰላም በመሆኑ የድሮን ጥቃት ስጋት ገሸሽ በማለቱ ነዋሪዎች መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ወደ ገበያም ያለ ስጋት እየወጡ ነው።