👉 ቋቁቻ (Pityriasis versicolor) ምንድነው?

ቋቁቻ የተለመደና በፈንገስ አማካኝነት የሚመጣ የቆዳ ህመም ነው

👉 ምልክቶቹ
ቋቁቻ በአብዛኛው ጀርባ ፣አንገት፣ደረትና የላይኛው የእጃችን ክፍል አካባቢ ይወጣል

ጠቆር ያሉ (hyperpigmented) ፣ ነጣ ያሉ (hypopigmented) አንዳንዴም ቀላ ያሉ ክብ ወይም እንቁላል ቅርጽ(oval) ሽፍታዎች ሲኖሩት እነዚህ ሽፍታዎች ላይም ትንንሽ ቅርፊቶች ይታያሉ

ሽፍታዎቹን በጣታችን ስንለጥጠው ወይም ፋቅ ፋቅ ስናረገው ቅርፊቶቹ በደንብ ይጎላሉ

የተለመደ ባይሆንም አንዳንዴ የማሳከክ ስሜት ሊኖር ይችላል

👉 ምን አይነት ሰዎች ላይ ይከሰታል
በአብዛኛው በወጣትነት እና በጎልማሳነት የእድሜ ክልል ውስጥ ይከሰታል

👉 ለቋቁቻ የሚያጋልጡን ሁኔታዎች

  • በተፈጥሮ ተጋላጭነት (genetic predisposition) ይህም በቤተሰብ አባላት ውስጥ እንዲከሰት ሊያደርግ ይችላል
  • ሞቃታማ አካባቢ መኖር
  • የበሽታ የመከላከል አቅም መዳከም
  • እርግዝና
  • ቆዳችን ወዛም ከሆነ
  • Oily የሆኑ ቅባቶችን መጠቀም
  • ከመጠን ያለፈ ላብ

👉 ቋቁቻ እንዴት ይታከማል?
ሽፍታው በቆዳ ሐኪም ታይቶ ከተረጋገጠ በኋላ ሐኪሙ በሚያዘው መሰረት በሚቀባ፣ በሻምፖ ወይም በሚዋጥ መድሀኒት ህክምናው ይሰጣል

ከህክምናው በኋላ ሽፍታው ላይ የነበሩት ቅርፊቶች ይጠፋሉ ይህም የህመሙን መዳን ያመለክታል

ነገር ግን ሽፍታው ወጥቶበት የነበረው ቦታ ወደ መደበኛው የቆዳችን ቀለም ለመመለስ ሳምንታትን/ወራትን ሊወስድ ይችላል

👉 ቋቁቻ ከሰው ወደሰው ይተላለፋል?
ቋቁቻ ከሰው ወደሰው አይተላለፍም

ለቋቁቻ መንስኤ የሆኑት የፈንገስ አይነቶች(በጥቅሉ Malassezia ተብለው ይጠራሉ) ከቆዳችን ጋር ተስማምተው የሚኖሩ (normal flora) ሲሆኑ ለህመሙ የሚያጋልጡን ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ወደ በሽታ አምጪነት የሚቀየሩ ናቸው፤ለዚህም ነው ህመሙ ደጋግሞ የሚከሰትብን

👉እንዴት እንከላከለው?

ቋቁቻ ደጋግሞ የሚከሰትብን ከሆነ እና በተለይም በሞቃታማ አካባቢ የምንኖር ከሆነ ከቆዳ ሐኪም ጋር በመመካከር ህክምናውን በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት ወይም በወር አንድ ጊዜ ለተወሰኑ ወራቶች በመውሰድ ቋቁቻ የሚመላላስበትን የጊዜ ፍጥነት መቀነስ ይቻላል

በተጨማሪም፡-

Oily የሆኑ ቅባቶችን አለመጠቀም

ከጥጥ የተሰሩ ልብሶችን መልበስ(በተለይ ከውስጥ የምንለብሳቸው)

ሰውነታችን ላይ የሚጣበቁ ልብሶችን አለማዘውተር

✔️ በመጨረሻም
ከቆዳ ሐኪም ውጪ የተሰሩ ቪድዮችን አይተን ወይም የቆዳ ሐኪም ሳናማክር መድሀኒቶችን ገዝተን ባለመጠቀም ቆዳችንን ከተጨማሪ ጉዳት እንከላከል‼️

በዶ/ር ዮሐንስ ታደሰ ፤ የቆዳና አባላዘር ህክምና ስፔሻሊስት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *